በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ባይደን እሥራዔል ገቡ፤ ሳዑዲ አረቢያንም ይጎበኛሉ


የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን፣ ቴል አቪቩ ውስጥ በሚገኘው በቤን ጉሪዮን አየር ማረፊያ ከደረሱ በኋላ የእሥራዔል ፕሬዚዳንት አይዛክ ሄርዞግ እና የመንግሥት ኃላፊዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል እአአ ሐምሌ 13/2022
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን፣ ቴል አቪቩ ውስጥ በሚገኘው በቤን ጉሪዮን አየር ማረፊያ ከደረሱ በኋላ የእሥራዔል ፕሬዚዳንት አይዛክ ሄርዞግ እና የመንግሥት ኃላፊዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል እአአ ሐምሌ 13/2022

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በመካከለኛው ምስራቅ ለሚያደርጉት ጉብኝት ዛሬ ረቡዕ እሥራዔል ገብተዋል።

ፕሬዚዳንቱ ዌስት ባንክንና የሳዑዲ አረብያን እንደሚጎበኙም ተዘግቧል።

ፕሬዚዳንቱ በመካከለኛው ምሥራቅ ቆይታቸው እሥራዔል ከክልሉ ጋር በጥብቅ እንድትተሳሰርና ለተፈጠረው ዓለምአቀፍ የኢነርጂ ቀውስ የፋርስ ባህረ ሰላጤ አገሮች ምላሽ ለመስጠት ተጨማሪ የከርሰ ምድር ዘይት እንዲያመርቱ ግፊት እንደሚያደርጉ ተነግሯል።

ምንም እንኳ የአሜሪካ ትኩረት በዩክሬን ጦርነትና ከቻይና ጋር ባለው የስትራተጂ ፉክክር ቢጠመድም አካባቢውን ችላ እንደማትል እንደሚገልፁም ይጠበቃል።

ባንድ ወቅት “ምንም የሚረባ ማኅበራዊ እሴት የለውም” ካሉት የሳዑዲ አገዛዝ ጋር ግንኙነቶቻቸውን ለማደስ ወደዚያ መሄዳቸው ከተሟጋቾችና ከራሳቸውም ፓርቲ አባላት የበረታ ወቀሳ አስነስቶባቸዋል።

የብሄራዊ ደኅንነት አማካሪው ጃክ ሱሊቫን “ግባችን ከሳዑዲ አረቢያ ጋር የነበረውን ግንኙነት ለማስተካከል እንጂ ለማቋረጥ አይደለም” ሲሉ ከትናንት በስተያ ሰኞ ለሪፖርተሮች ተናግረዋል። “አካባቢያዊ የፖለቲካ ፉክክር በተለይ ደግሞ በኢንዶፓሲፊክና በአውሮፓ እጅግ እየተስፋፋ በመጣበት በዚህ ጊዜ ዩናይትድ ስቴትስ በመካከለኛው ምሥራቅ ያላትን ተሣትፎ አጠናክራ መቆየት አለባት” ሲሉ ሱሊቫን ተከራክረዋል።

አክለውም “መካለኛው ምሥራቅ ከቀሪው የዓለም ክፍል ጋር በእጅጉ ተቆራኝቷል። ስለዚህ አሁን ሰላማዊና የተረጋጋ አካባቢ የመፍጠር እምርጃዎችን ብንወሰድ በሚመጡት ዓመታት ለአሜሪካ ብሄራዊ ጥቅምና ለአሜሪካ ህዝብ የሚተርፍ ውጤት ያስገኛል" ብለዋል አማካሪው።

ባይደን በእሥራዔል ቆይታቸው መንግሥቱን በሞግዚትነት ከሚያስተዳደሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ያሪ ላፒድና ከተቃዋሚው መሪ ቤንጃሚን ኔታኒያሁ ጋር ተገናኝተው ከባህረ ሰላጤው የአረብ አገሮች ጋር የአየር መከላከያ አቅምን ማቀናጀትን በሚቻልበት ሁኔታና በማንሠራራት ላይ ስላለችው ኢራን እንዲሁም በእሥራዔል ደህንነት ዙሪያ ይመክራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ፕሬዚዳንቱ በዌስት ባንክ ቆይታቸው ወቅት ለእሥራዔል ፍልስጥዔም ችግር የሁለት መንግሥታት ምሥረታ መፍትኄን እንደሚደግፉ በድጋሚ እንደሚያረጋግጡና ከፍልስጥዔም ባለሥልጣናት ጋርም ሃገራቸው የነበራትንና በትረምፕ አስተዳደር ዘመን የተበላሸውን ግንኙነት ለማደስ እንደሚጥሩ ተገልጿል።

XS
SM
MD
LG