በሆሊውድ የሚገኙ የፊልምና የቴሌቭዥን ፕሮግራም ጸሃፊዎች የክፍያ ጭማሪና አስተማማኝ የሥራ ሁኔታን በመጠየቅ አድማ በመምታታቸው፣ የምሽት የቴሌቭዥን ፕሮግራሞችና የፊልም ፕሮጀክቶች ላልተወሰነ ግዜ ሲቋረጡ፣ በአጠቃላይ የፊልም ኢንዱስትሪው እንዲያዘግም አድርጓል፡፡
ከአስራ አምስት ዓመታት በኋላ የተደረገ ነው በተባለው የጸሃፊዎች የሥራ ማቆም አድማ 11ሺሕ 500 የሚሆኑና ራይተርዝ ጊልድ ኦፍ አሜሪካ የተሰኘው ማኅበር ዓባላት ባለፈው ማክሰኞ ኮንትራታቸው በሚያበቃበት ዕለት የሥራ ማቆም አድማ መተዋል፡፡
ከጥያቄዎቻቸው መካከልም፣ የዝቅተኛ ክፍያ መጨመር እና በአንድ ፕሮግራም ላይ በርካታ ጸሃፊዎች መሣተፍ የሚሉት ይገኙበታል፡፡
የጸሃፊዎቹ ኅብረት በተጨማሪም የፊልም አዘጋጆች ሥራቸውን ለማጠናቀቅ አቋራጭ መንገድ ይሠጣቸዋል ያሉት ‘የሠው ሰራሽ ልዕቀት’ ወይም አርቲፊሺያል ኢንተሊጀንሥ ቁጥጥር እንዲደረግበት ጠይቀዋል፡፡
የጸሃፊዎቹን አድማ በመደገፍ አንዳንድ ተዋንያንም ተሳትፈዋል፡፡ ጃሽ ጋድ የተባለው ተዋናይ “ካለ ጸሃፊዎቹ እኛ ምንም አይደለንም። ጥያቄዎቻቸው መመለስ አለባቸው ሲል ተደምጧል፡፡”
ከአስራ አምስት ዓመታት በፊት በተደረገ ተመሣሣይ አድማ የጸሃፊዎቹን ጥያቄዎች ለመመለስና አድማውን ለማቆም ሦስት ወራትን ፈጅቷል፡፡
‘የተንቀሳቃሽ ምስሎችና የቴሌቭዥን አዘጋጆች አንድነት’ የተሰኘውና ስቱዲዮችንና የፊልም ዝግጅት ኩባንያዎችን የሚወክለው ማኅበር ባወጣው መግለጫ፣ ዳጎስ ያለ ክፍያ ለመስጠት የተስማማ ቢሆንም፣ ጸሃፊዎቹ ሌሎች ከበድ ያሉ ጥያቄዎች ስላሏቸው ያንን ተግባራዊ ለማድረግ አለመቻሉን አስታውቋል፡፡