በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የአሜሪካ ሕግ አውጪዎች የኢራን አብዮታዊ ዘብ በአሸባሪነት እንዲፈረጅ ጠየቁ


ፎቶ ፋይል፦ የኢራን አብዮታዊ ዘብ
ፎቶ ፋይል፦ የኢራን አብዮታዊ ዘብ

የአውሮፓ ኅብረት፣ የኢራን አብዮታዊ ዘብን በአሸባሪነት እንዲፈርጅ፣ ከኹለቱም የፖለቲካ ፓርቲዎች የተውጣጡ፣ ከ130 በላይ የዩናይትድ ስቴትስ የምክር ቤት አባላት ፈርመው በአወጡት የጋራ ደብዳቤ ጠየቁ።

“ኢራን፣ ሽብርተኝነትን ከሚደግፉ መንግሥታት ግንባር ቀደሟ ናት፤” ያለው የሕግ አውጭዎቹ ደብዳቤ የተላከው፣ ለአውሮፓ ኅብረት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ሓላፊ ጆሴፍ ቦሬል እንደኾነ ተገልጿል።

“የኢራን አብዮታዊ ዘብ፣ ለዐሥርት ዓመታት፣ በመላው የአውሮፓ አህጉር ዜጎችን ዒላማ ያደረጉ የሽብር ጥቃቶችን ያለከልካይ ሲያካሒድ ቆይቷል፤” ሲልም የሕግ አውጪዎቹ ደብዳቤ አመልክቷል።

“የኢራን አብዮታዊ ዘብን በአሸባሪነት ለመፈረጅ፣ የአውሮፓ ኅብረት የጋራ አቋም ሕግ ቁጥር 931ን ውስብስብነት እንገነዘባለን፡፡ ውሳኔው፥ ተገቢው ሥልጣን ባለው የፍትሕ አካል እንዲወሰን ያለውንም ፍላጎት ሙሉ ለሙሉ እናደንቃለን፤” ያለው የሕግ አውጭዎቹ ደብዳቤ፣ “ይኹን እንጂ፣ ኢራን በአውሮፓ ኅብረት አባል አገሮች እና ዜጎች ላይ የደቀነችው አደጋ እየጨመረ ከመምጣቱ አንጻር፣ ይህን ጉዳይ በአስቸኳይ እንዲመለከቱት እናሳስብዎታለን፤” ብሏል።

ደብዳቤው አክሎም፣ ኢራን ባለፉት አምስት ዓመታት፣ በአውሮፓ ውስጥ ዜጎችን ለመከታተል፣ ለማገት ወይም ለመግደል ቢያንስ 33 የሚደርሱ ሤራዎችን ጠንስሳለች፤ ሲል ዌስት ፖይንት የተባለው ሽብርተኝነት የሚዋጋ ማዕከል ያወጣውን ጥናትም ጠቅሷል።

ቦሬል፣ “የኢራንን አብዮታዊ ዘብ በሽብርተኝነት ለመፈረጅ፣ ቢያንስ፣ የአውሮፓ ኅብረት አባል በኾነ አንድ አገር ከሚገኝ ፍርድ ቤት፣ የውግዘት ውሳኔ መውጣት ይኖርበታል፤” ብለዋል።

ዩናይትድ ስቴትስ፣ የኢራንን አብዮታዊ ዘብ በአሸባሪነት የፈረጀቸው፣ እ.ኤ.አ በ2019 እንደነበረ በመረጃው ተመልክቷል።

XS
SM
MD
LG