ዋሽንግተን ዲሲ —
ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በኮሎራዶ ክፍለ ግዛት ቦልደር ወረዳ ውስጥ ትናንት ሀሙስ የተነሳው ሰደድ እሳት 580 ቤቶችን የገበያ ማዕከልና ከዴንቨር ከተማ ወጣ ብሎ የሚገኝን አንድ ሆቴል ማውደሙ ተነገረ፡፡
ባለሥልጣናት 21ሺ ሰዎች ይኖሩባታል የተባለቸው የሉዊስቪል ከተማና 13ሺ ነዋሪዎች ያሏት የሱፒሪየር ከተማ ነዋሪዎች ከተሞቻቸውን ለቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ ማስተላለፋቸው ተገልጿል፡፡
የቦልደር ወረዳ ሸሪፍ እሳካሁን ቢያንስ አንድ ሰው መሞቱን ገልጸው ሰባት ሰዎች መቁሰላቸውን አስታውቀዋል፡፡ በሰዓት 170 ኪሎሜትር በሚገፋው ነፋስ ይታገዝ የነበረው የሰደድ እሳት ብዙ ሞትና ጉዳት ያደርስ እንደነበርም ኃላፊው ገልጸዋል፡፡
በሰደድ እሳት ጉዳት የደረሰበት አካባቢ ከቦልደር እስከ ዴንቨር አካባቢ ያለው ስፍራ ሲሆን የኮሎራዶ ዩኒቨርስቲ የሚገኝበት አካባቢ መሆኑም ተመልክቷል፡፡