የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የጀርመኑን ቻንስለር ኦላፍ ሾልዝ ዛሬ በዋይት ሃውስ ተቀብለው እንደሚያነጋግሩ ይጠበቃል። ውይይታቸውም ለዩክሬን በሚሰጠው ድጋፍና በሌሎች ዓለም አቀፍ የጸጥታና የኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ እንደሚያተኩር ተገልጿል።
ሁለቱ መሪዎች መጀመሪያ የተገናኙት ባለፈው የካቲት ሾልዝ በጀርመን ሥልጣኑን በተቆናጠጡበት ወቅት ሲሆን፣ የአሁኑ ጉብኝታቸው ደግሞ ሩሲያ በዩክሬን ላይ የፈጸመችው ወረራ አንደኛ ዓመት እንደሞላው የተደረገ መሆኑ ነው።
“በጦርነቱ ወቅት ለዩክሬን የምንሠጠውን ድጋፍ በመቀናጀት ስናደርግ ቆይተናል፣ ይህም ባለፈው ወር ለእግረኛ ጦር የሚያገለግሉ ተሽከርካሪዎችን እንደምንሰጥ በጋራ ያስታወቅንበትን ይጨምራል” ሲሉ የአሜሪካው ብሄራዊ የጸጥታ ም/ቤት ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢ ትናንት ለዜና ሠዎች ተናግረዋል።
ጀርመን እስከ አሁን ከፍተኛ ቁጥር ያለው የጦር መሳሪያ ለዩክሬን እንደለገሰች ኪርቢ ጨምረው አስታውቀዋል።
ተጨማሪ ዕርዳታ ለዩክሬን የሚሠጥበት ጉዳይ ለሁለቱ መሪዎች ዋና የመነጋገሪያ አጀንዳ ይሆናል ብለዋል ኪርቢ።
ለጀርመን ፓርላማ ትናንት ሐሙስ ንግግር ያደረጉት ሾልዝ፣ ቻይና ያላትን ተጽዕኖ በመጠቀም ሩሲያ ከዩክሬን እንድትወጣ እንድታግባባና መሣሪያም እንዳትሰጥ ጥሪ አድርገዋል።
ቻይና ለሩሲያ የምትሰጠው የመሣሪያ ድጋፍ አሳሳቢ መሆኑን አሜሪካ በይፋም ሆነ በቀጥታ ለቻይና ግልጽ ድርጋለች ሲሉ የአሜሪካው ብሄራዊ የጸጥታ ም/ቤት ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢ ጭምረው ተናግረዋል።