በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የዩክሬን ፕሬዚዳንት ከአውሮፓ ሀገሮች ተጨማሪ እርዳታ እየጠየቁ ናቸው


የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎዶሚር ዘለንስኪ ትናንት ወደምስራቋ ካርኪቭ ከተማ ተጉዘው በዚያ ያሉ የዩክሬን ኃይሎችን ሲጎበኙ እአአ ግንቦት 29/2022
የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎዶሚር ዘለንስኪ ትናንት ወደምስራቋ ካርኪቭ ከተማ ተጉዘው በዚያ ያሉ የዩክሬን ኃይሎችን ሲጎበኙ እአአ ግንቦት 29/2022

የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎዶሚር ዘለንስኪ ዛሬ ለአውሮፓ ምክር ቤት ንግግር ያደርጋሉ። ለሀገራቸው ተጨማሪ እርዳታ እንዲሰጥ እና ሩሲያ ወረራዋን እንድታቆም በይበልጥ የበረታ ግፊት እንዲደረግባት የሚጠይቁ መሆኑ ተገልጿል።

ለሁለት ቀናት ከሚካሄደው ስብሰባ አስቀድመው የአውሮፓ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሻርል ሚሼል በጻፉት ደብዳቤ በአንገብጋቢነት የሚያሳስበን ጉዳይ የዩክሬይን መንግሥት ላለበት የበጀት ችግር ድጋፍ መስጠት ሲሆን ከዓለም አቀፍ አጋሮቻችን ጋር ሆነን ለሀገሪቱ መልሶ ግንባታ የምናደርገውን ድጋፍ እንዴት ማደራጀት እንዳለብን እንወያያለን ብለዋል። ከሩሲያ ወረራ ባስከተለው የነዳጅ እና የምግብ ዋጋ ውድነት ዙሪያም ውይይት እንደሚካሄድ ጠቅሰዋል።

በውጊያው ግንባር የሩሲያ ኃይሎች በሉሃንስክ ክፍለ ግዛት በዩክሬይን ኃይሎች እጅ የነበረችውን የመጨረሻዋን ከተማ ሲቬሮዶኒትስክን ተቆጣጥረዋል። የዩክሬን ፕሬዚዳንት ትናንት ማታ ባደረጉት ንግግራቸው

“ወራሪው ኃይል ከተማዋን ለመያዝ ተነስቷል፤ የቻልነውን ሁሉ አድርገን እንከላከላለን" ብለው ነበር። ዘለንስኪ አያይዘው የሩሲያ ኃይሎች የከተማዋን ዘጠና ከመቶውን ህንጻዎች አውድመዋል፣ አብዛኛውን የመኖሪያ ቤት አፈራርሰዋል፥ የቴሌኮሙኒኬሽን መስመሮች ቆራርጠዋል ብለዋል።

በሌላ በኩል የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ለአንድ የፈረንሳይ ቴሌቭዢን ትናንት በሰጡት ቃል ዶኔትስክ እና ሉሃንስክን ነጻ ማውጣት ሩሲያ ቅድሚያ የምትሰጠው ጉዳይ ነው ብለዋል። ሀገራቸው ሁለቱን አካባቢዎች ነፃ ሀገር አድርጋ እንደምትመለከት ነው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የገለጹት።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የዩክሬኑ ከዋና ከተማዋ ከኪየቭ ውጭ አዘውትረው የማይጓዙት ፕሬዚዳንት ዜሌንስኪ ትናንት ወደምስራቋ ካርኪቭ ከተማ ተጉዘው በዚያ ያሉ የዩክሬን ኃይሎችን ጎብኝተዋል። ተዋጊዎቹን አመስግነዋል።

XS
SM
MD
LG