ዩናይትድ ስቴትስ በሙስና በተወነጀሉ ሦስት የላይቤሪያ መንግሥት ባለሥልጣናት ላይ ማዕቀብ ጥላለች።
ማዕቀቡ ከተደነገገባቸው አንዱ የላይቤሪያ ፕሬዚዳንት ጆርጅ ዊያ ፅህፈት ቤት ሹም ናታኒየል መጊል፤ እንዲሁም ሌሎቹ ሁለት ባለሥልጣናት ጠቅላይ አቃቤ ህጉ ሳይሬኒየስ ሴፈስና የብሄራዊ ወደቦች አገልግሎት ዳይሬክተሩ ቢል ቲዌዌ መሆናቸውን የዩናይትድ ስቴትስ የገንዘብ ሚኒስቴር ትናንት፤ ሰኞ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
የገንዘብ ሚኒስቴሩ መግለጫ አክሎም ማዕቀቡ ዩናይትድ ስቴትስ ሙሰኛ ባለሥልጣናትን በተጠያቂነት ለመያዝ ያላትን ቁርጠኛነትና የላይቤሪያን ህዝብ መደገፏን እንደምትቀጥል የሚያሳይ መሆኑን አመልክቷል።
ሦስቱ ባለሥልጣናት የመንግሥት ገንዘብና ንብረት ያለአግባብ ወይም ለግል ጥቅም በማዋልና ጉቦ መብላትን ጨምሮ በሙሰኛነት የተመዘገቡ መሆናቸውን መግለጫው አመልክቷል።