ግጭቶችን ለመከላከልና ሲከሰቱም እንዲቆሙ ለማድረግ፣ የልማት ጥረቶችን ለማጎልበትና የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን ጣጣ ለመቀነስ በሚወጠኑ ጅምሮች ምክንያት ዓለምን ዞረዋል።
በጉዟቸውም ከበርካታ መሪዎች ጋር ተገናኝተው በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረጉትን ያህል ከቀያቸው ተፈናቅለው ለመሰደድ የተገደዱ ብዙዎችንና እንዲሁም በከፉ የተፈጥሮ አደጋዎች ሣቢያ ለውድመት የተጋለጡ ወገኖችን በያሉበት ጎብኝተዋል።
በአመራር ዘመናቸው የሠሩ ወይም ያልሠሩትን አስመልክቶ ትተውት ስለሚሄዱት ቅርስ ብይን የሚሰጡት የታሪክ አዋቂዎች መሆናቸውን ያስታወሱት ባን ኪ-ሙን ከክንውኖቻቸው ሁሉ የላቀ ሥፍራ የሚሰጡት ግን ረሃብን ለማጥፋት ለታለመው ባለ አሥራ ሰባት ነጥብ የዘላቂ ልማት ግቦች እቅድ መሆኑን ይናገራሉ።
የደቡብ ኮሪያ ተወላጁ ባን ኪ-ሙን ሰሜን ኮሪያ በተደጋጋሚ በምታደርገው የኒኩሌር እና የተምዘግዛጊ ሚሳይሎች የሙከራ ውንጨፋዎች ሳቢያ እየከረረ በመጣው የኮሪያ ልሳነ-ምድር ውጥረት ቀልባቸው እንደተያዘ ነው።
ባለፈው ዓመት ሰሜን ኮሪያን ለመጎብኘት ይዘውት የነበረውን የጉዞ ዕቅድ በመጨረሻ ደቂቃ ፒዮንግያንግ በመሠረዟ ተስተጓጎለ።
ባን በዓለም ዙሪያ የሞት ቅጣት እንዲቆም፥ የሴቶችን መብቶች ጥበቃ ለማሻሻል እና ብጥብጦችን ለመዋጋት የመንግሥታቱ ድርጅት ባደረገው ጥረት ይወደሳሉ።
ለተጨማሪ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ፡፡