የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት፣ የፍልስጤም ራስ ገዝ የተመድ አባል ለመሆን ባቀረበው ጥያቄ ላይ ዛሬ ድምፅ እንደሚሰጥ ይጠበቃል።
የምክር ቤቱን ሙከራ፣ የእስራኤል አጋር የሆነችው አሜሪካ እንደምትገታው ይጠበቃል። ምክንያቱ ደግሞ፣ ውሳኔው የሚሰጥ ከሆነ፣ ፍልስጤምን እንደ ሃገር እውቅና መስጠት ስለሚሆን ነው ተብሏል።
አስራ አምስት አባላት ያሉት የፀጥታው ምክር ቤት፣ 193 አባላት ያሉት የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ጉዳዩን እንዲመለከት ሐሳብ በሚያቀርበው ረቂቅ የውሳኔ ሐሳብ ላይ ዛሬ ድምፅ እንደሚሰጥ ዲፕሎማቲክ ምንጮችን ጠቅሶ ሮይተርስ ዘግቧል።
የፀጥታው ምክር ቤት አንድን የውሳኔ ሃሳብ ለማሳለፍ ቢያንስ በዘጠኝ ድምፆች መደገፍ ያለበት ሲሆን፣ ድምፅን በድምፅ የመሻር መብት ካላቸው አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሣይ፣ ሩሲያ እና ቻይና ደግሞ ተቃውሞ ሊገጥመው አይገባም።
በእ.አ.አ 2012 ጠቅላላ ጉባኤው በወሰነው መሠረት፣ ፍልስጤማውያን በአሁኑ ወቅት አባል ያልሆነ የታዛቢነት ተሳተፎ የሚያደርጉ ሲሆን፣ የተመድ ዓባል ለመሆን በፀጥታው ም/ቤት ሙሉ ድጋፍ ማግኘት እና በጠቅላላ ጉባኤው ደግሞ ቢያንስ ሁለት ሶስተኛ ድጋፍ ማግኘት አለበት፡፡
የፍልስጤማውያኑ የተመድ ዓባልነት ጥያቄ የመጣው፣ በእስራኤል እና በሐማስ መካከል የሚካሄደው ጦርነት ስድስት ወራትን ባስቆጠረበትና፣ እስራኤል በያዘችው ዌስት ባንክ ሰፈራዋን በማስፋፋት ላይ ባለችበት ወቅት ነው።
መድረክ / ፎረም