በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

“የሚጥለው ዝናም መልካም ቢኾንም ጎርፉ ኮሌራን እያስፋፋ ነው” - ኦቻ


“ባለፈው አንድ ሳምንት ብቻ 51 ሰዎች በኮሌራ ሞተዋል”

በአሁኑ ወቅት እየጣለ ያለው የተዛባ ዝናም፣ ለሰዎችም ኾነ ለእንስሳት መጠጥ የሚኾን ውኃ እያስገኘ ቢኾንም፣ በአንዳንድ ቦታዎች ግን የሚያስከትለው ጎርፍ፣ የኮሌራን መዛመት እያባባሰ መኾኑን፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ ርዳታ ማስተባበሪያ ቢሮ(ኦቻ) አስታውቋል።

የድርቁ ኹኔታም የቀጠለባቸው አካባቢዎች እንዳሉ የጠቀሰው ኦቻ፣ በድርቅ በተጠቁም ኾነ ባልተጠቁ የኦሮሚያ፣ የሶማሌ እና የአፋር ክልሎች፣ እየጣለ ያለው ከባድ ዝናም እና የሚያስከትለው ጎርፍ፣ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮችን መጠለያ ሲያፈርስ፣ የእንስሳትን ሕይወት ቀጥፏል፤ እንዲሁም፣ ቀድሞውንም በከፍተኛ ፍጥነት በመዛመት ላይ ያለውን ኮሌራ ማባባሱን፤ በመግለጫው አትቷል። በመኾኑም፣ “አፋጣኝ ምላሽ ይሻል፤” ሲል አሳስቧል።

ዝናሙ፣ በድርቅ በተጠቁ የኦሮሚያ እና የሶማሌ ክልሎች በሚገኙ፣ የመጸዳጃ አገልግሎት እጥረት ባለባቸው ወይም አገልግሎቶቹ ጨርሶ በሌለባቸው አንዳንድ አካባቢዎች፣ ኮሌራ በፍጥነት እንዲዛመት ማድረጉን ኦቻ ጠቅሷል፡፡ ባለፉት ሦስት ሳምንታት፥ በቦረና ዞን፣ ሰባት ሰዎች በኮሌራ መያዛቸው ሲታወቅ፤ በኦሮሚያ ክልል 2ሺሕ62፣ በሶማሌ 308፣ በድምሩ 2ሺሕ370 ሰዎች በኮሌራ መጠቃታቸውን አስታውቋል።

የሕሙማኑ ቁጥር፣ ቀደም ካሉት ሳምንታት ጋራ ሲነጻጸር፣ 50 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱንና ባለፈው አንድ ሳምንት ውስጥ ብቻ 51 ሰዎች በኮሌራ እንደሞቱ፣ የኢትዮጵያ የሕዝብ ጤና ተቋምን ጠቅሶ፣ ኦቻ በመግለጫው አመልክቷል።

ኦቻ አያይዞም፣ ለችግሩ እየተሰጠ ባለው መፍትሔ፣ በኹለቱ ክልሎች ኹለት የኮሌራ ሕክምና ማዕከላት ሲቋቋሙ፣ የውኃ ማጣራት ሥራዎችም ተሠርተዋል፤ የኮሌራ ክትባት ዘመቻም ተደርጓል፤ ብሏል።

XS
SM
MD
LG