ዋሺንግተን ዲሲ —
የተባበሩት መንግሥታት የህፃናት መርጃ ድርጅት /ዩኒሴፍ/ ሃገራት የክትባት ተደራሽነት እንዳይቀርባቸው ለማድረግ በቀጣዩቹ ሁለት ዓመታት የኮቪድ-19 ክትባቶችን ከሚሰሩ ኩባኒያዎች የመግዛትና የማከፋፈል ሂደት ኃላፊነቱን እንደሚመራ አስታወቀ።
ዩኒሴፍና የዓለም የጤና ድርጅት በጋራ ሆነው እስካሁን በግዝፈቱ እና በፍጥነቱ ወደር የሌለው የሚሆነውን ክትባት ማዳረስ መርኃ ግብር እንደሚመሩ አስታውቀዋል።
ዩኒሴፍ ትናንት ባወጣው መግለጫ “ኮቫክስ” በሚል የእንግሊዝኛ አህፅሮት የሚጠራው መርኃ ግብር ለዘጠና ሁለት የዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ሃገሮች ክትባቶቹን እኩል ለማዳረስ የታለመ መሆኑን ገልፆ በመርኃ ግብሩ ሰባ ስድስት ባለፀጋ ሃገሮች ሊሳተፉ መስማማታቸውን አስታውቋል።
ዩናይትድ ስቴትስ መርኃ ግብሩን የሚመራው ለቻይና ወገንተኛ ብላ የምትከሰው የዓለም የጤና ድርጅት በመሆኑ አልሳተፍም ስትል በዚሁ ሳምንት ውስጥ አስታውቃለች።