በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በሶማሊያ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ህፃናት በቸነፈር ሊያልቁ ይችላሉ ተባለ


ፎቶ ፋይል፦ ፋጡማ አብዲ አሊዮው የተባለች እናት ሶማሊያ ሞቃዲሾ ወጣ ብሎ በሚገኝ የተፈናቃዮች መጠለያ ካምፕ ውስጥ በተመጣጠነ ምግብ እጥረት የሞቱ ሁለት ልጆቿ መቃብር አጠገብ ተቀምጣ፡፡
ፎቶ ፋይል፦ ፋጡማ አብዲ አሊዮው የተባለች እናት ሶማሊያ ሞቃዲሾ ወጣ ብሎ በሚገኝ የተፈናቃዮች መጠለያ ካምፕ ውስጥ በተመጣጠነ ምግብ እጥረት የሞቱ ሁለት ልጆቿ መቃብር አጠገብ ተቀምጣ፡፡

በሶማሊያ ከዚህ በፊት ባልታየ ቁጥር የገዘፈ የህፃናት ሞት ሊከሰት ይችላል ሲል የተባበሩት መንግሥታት የህፃናት አድን ድርጅት (ዩኒሴፍ) ዛሬ አስጠንቅቋል።

የድርጅቱ ቃል አቀባይ ጄምስ ኤልደር ከጄኔቭ በሰጡት መግለጫ በሶማሊያ በየቀኑ፣ በእያንዳንዷ ደቂቃ አንድ ህፃን በከባድ የተመጣጠነ ምግብ ዕጦት ምክንያት ደክሞ ወደ ጤና ጣቢያ ይወሰዳል ብለዋል።

የቅርብ አሃዞች እንደሚያመለክቱት፣ ባለፈው ነሐሴ ወር ብቻ 44 ሺህ ህፃናት ከተመጣጠነ ምግብ ዕጦት ጋር በተየያዘ ወደ ጤና ጣቢያ ለህክምና ተወስደዋል ሲሉ ቃል አቀባዩ ጨምረው ተናግረዋል። ይህም በእያንዳንዱ ደቂቃ አንድ ህፃን መሆኑ ነው ብለዋል።

እነዚህን ህፃናት ወደ ጤና ጣቢያ ለማምጣት እናቶች ለቀናት እንደሚጓዙና፣ ህፃናቱም እጅግ ተዳክመው እንደሚደርሱ ዩኒሴፍ አስታውቋል።

በተመጣጠነ ምግብ የተጠቁ ህፃናት በተቅማጥና ኩፍኝ የመሞት ዕድላቸው በ11 ዕጥፍ እንደሚጨምርም የህፃናት አድን ድርጅቱ ገልጾ፣ እነዚህ አመላካቾች በሶማሊያ ከዚህ በፊት ያልታየ እልቂት እንደሚኖር የሚያስጠነቅቁ ናቸው ሲሉ ቃል አቀባዩ ጄምስ ኤልደር ጨምረው ገልጸዋል።

በአሸባሪዎች እንቅስቃሴና በዕርዳታ ሠራተኞች ላይ በተጋረጠው እንቅፋት ምክንያት፣ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ህፃናት የጤና አገልግሎት ወዳለበት መሄድ ስለማይችሉ፣ የተጎጂዎቹ ቁጥር በይፋ ከተገለጸው በእጅግ እንደሚጨምር ቃል አቀባዩ አመልክተዋል።

“አሁን በሶማሊያ ያለው ሁኔታ” ይላሉ ጄምስ ኤልደር “በእአአ 2011 260 ሺህ ሰዎች ከሞቱበት ቸነፈር የባሰ ነው። ከፍተኛ የሆነ ምላሽ ካልተሰጠና አስፈላጊው መዋዕለ ነዋይ ካልተመደበ በግማሽ ምዕተ ዓመት ታይቶ የማይታወቅ የህፃናት እልቂት ይኖራል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

XS
SM
MD
LG