በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

“አያሌ ሕፃናት ለመከላከል በሚቻሉ በሽታዎች የመሞት አደጋ ተደቅኖባቸዋል” ዩኒሴፍ


የጤና ባለሞያዋ የፖልዮ ክትባት ለታዳጊዎች ሲሰጡ ላሆሪ ፓኪስታን እአአ ጥቅምት 24/2022
የጤና ባለሞያዋ የፖልዮ ክትባት ለታዳጊዎች ሲሰጡ ላሆሪ ፓኪስታን እአአ ጥቅምት 24/2022

በዓለም አቀፉ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት፣ የመደበኞቹ ክትባቶች አሰጣጥ በመቀነሱ የተነሣ፣ በብዙ ሕፃናት ላይ ለማስቀረት በሚቻሉ በሽታዎች የመሞት አደጋ ተደቅኗል፤ ሲል ዩኒሴፍ አስጠነቀቀ፡፡

የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት እአአ የ2023 የዓለም ሕፃናትን ኹኔታ አስመልክቶ በአወጣው ሪፖርቱ፣ ጥናት ከተካሔደባቸው 55 ሀገራት ውስጥ፣ በ52ቱ፥ ለሕፃናት ክትባት አስፈላጊነት የሚሰጠው ትኩረት መቀነሱን ገልጿል፡፡ በደቡብ ኮሪያ፣ በጋና፣ በሴኔጋል፣ በጃፓንና በፓፓዋ ኒው ጊኒ፣ የሕፃናት ክትባት አሰጣጥ፣ ከአንድ ሦስተኛ በሚበልጥ መጠን መቀነሱን ዩኒሴፍ ተናግሯል፡፡

በጥናቱ፣ ስለ ክትባት ጠቃሜታ አዎንታዊ አመለካከት እንደያዙ የጸኑት ሦስት ሀገራት ብቻ እንደኾኑ ሲገጠቀስ፤ እነርሱም፥ ቻይና፣ ሜክሲኮ እና ሕንድ ብቻ መኾናቸውን ሪፖርቱ አያይዞ ጠቁሟል፡፡

ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወዲህ፣ በብዙ ሀገራት፣ ዕድሜያቸው ከ35 ዓመት በታች የኾኑ ሰዎች ዘንድ፣ ስለ ክትባት ጠቃሜታ ያላቸው እምነት፣ ከተቀሩት ይበልጥ ዝቅተኛ ኾኖ መገኘቱን አመልክቷል፡፡ በዓለም ውስጥ፣ 67 ሚሊዮን ሕፃናት፣ አንድ ወይም ከአንድ በላይ መደበኛ ክትባት ሳይከተቡ በቀሩበት በዚኽ ወቅት፣ አሳሳቢ እንደኾነ ሪፖርቱ አስገንዝቧል፡፡

ለሦስት ዓመታት በዘለቀው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሳቢያ፣ የመደበኞቹ ክትባቶች ክንዋኔ በመደናቀፉ የተነሣ፣ አስፈላጊውን ክትባት ሳያገኙ ከቀሩት ከ67 ሚሊዮኑ ሕፃናት ውስጥ ቢያንስ ግማሹን አኀዝ የሚይዙት፣ የአፍሪካ ሀገራት እንደኾኑ፣ የዩኒሴፍ ሪፖርት አመልክቷል፡፡

XS
SM
MD
LG