በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በሱዳን ጦርነት ወደ ስምንት ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ተፈናቅለዋል - ተመድ


በሱዳን ጦርነት ወደ ስምንት ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ተፈናቅለዋል - ተመድ
please wait

No media source currently available

0:00 0:01:53 0:00

በሱዳን ጦርነት ወደ ስምንት ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ተፈናቅለዋል - ተመድ

በሱዳን ተቀናቃኝ ጀነራሎች መካከል በተነሳው ጦርነት የተፈናቀሉት ሰዎች ቁጥር ወደ ስምንት ሚሊየን እንደሚጠጋ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ረቡዕ እለት አስታውቋል።

በኢትዮጵያ ጉብኝት እያደረጉ የሚገኙት፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነር ፍሊፖ ግራንዲ፣ የስደተኞቹን "ፍላጎት ለሟሟላት አስቸኳይ እና ተጨማሪ ድጋፍ እንዲደረግ" ጥሪ ማቅረባቸውንም ድርጅቱ ያወጣው መግለጫ አመልክቷል።

በሱዳን ጦር መሪ አብደል ፈታህ አል-ቡርሃን እና ምክትላቸው በነበሩት የፈጥኖ ደራሽ ሠራዊት አዛዥ ጄነራል ሞሃመድ ሃምዳን ዳጋሎ መካከል ግጭት የተቀሰውቀሰው ሚያዚያ ወር አጋማሽ ነበር።

ጦርነቱን ለማስቆም ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ቢቀጥሉም፣ በርካታ የተኩስ አቁም ስምምነቶች በመፍረሳቸው እስካሁን ፍሬ ማፍራት አልቻሉም። በመሆኑም 'አሰቃቂው ግጭት' ወደ ስምንት ሚሊየን የሚጠጉ ሰዎች በአገር ውስጥ እንዲፈናቀሉ ወይም ወደሌሎች አገሮች እንዲሰደዱ ማድረጉን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ገልጿል።

የድርጅቱ መግለጫ ላይ የተጠቀሱት ግራንዲ "በቤተሰብ፣ በጓደኛ፣ በመኖሪያ ቤት እና በመተዳደሪያ ላይ የደረሱ እጅግ ልብ የሚሰብሩ የማጣት ታሪኮችን ሰምቻለሁ" ብለዋል።

ከስደተኞቹ መካከል ከ100 ሺህ በላይ የሚሆኑት፣ ስደተኞቹን ካስጠለሉት ስድስት የጎረቤት አገሮች አንዷ ወደሆነችው ኢትዮጵያ መግባታቸውን የመንግሥታቱ ድርጅት ግምት ያሳያል።

ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ ወደ ቻድ የሄዱት ሰዎች ቁጥርም ባለፈው ሳምንት ከ500 ሺህ የበለጠ ሲሆን፣ በየቀኑ በአማካይ 1ሺህ 400 የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ ወደ ደቡብ ሱዳን እንደሚሰደዱ የመንግሥታቱ ድርጅት መግለጫ አመልክቷል።

"ለጋሾች ተጨማሪ ድጋፍ የማያደርጉ ከሆነ፣ ከፍተኛ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ድጋፍ ማድረግ እጅግ አስቸጋሪ ይሆናል" ሲሉ ግራንዲ ተናግረዋል።

በሱዳን ጦርነት ቢያንስ 13 ሺህ ሰዎች መገደላቸውን የግጭት ቦታ እና ክንዋኔዎችን የሚሰበስብ አንድ ፕሮጀክት ያጠናከረው መረጃ ያመለክታል።

በጦርነቱ የተሳተፉ ሁሉም ወገኖች፣ በመኖሪያ አካባቢዎች ላይ ድብደባ ማካሄድ፣ ማሰቃየት እና ሰላማዊ ዜጎችን በዘፈቀደ ማሰርን ጨምሮ፣ የጦር ወንጀል ክስ ይቀርብባቸዋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG