የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነር በምኅጻሩ ዩ.ኤን.ኤች.ሲ.አር፣ ባለፈው ሐምሌ ወር፣ ከአጋሮች ጋራ በመተባበር፣ “በዘፈቀደ የታሰሩ” ያላቸውን በመቶዎች የሚቆጠሩ የከተማ ውስጥ ስደተኞችን ማስፈታቱን አስታውቋል፡፡
ዩ.ኤን.ኤች.ሲ.አር፣ ከትላንት በስቲያ ሰኞ ባወጣው ሪፖርት፣ በዐዲስ አበባ 879 ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ያቀረቧቸውን አስተያየቶች እና ቅሬታዎች መሠረት በማድረግ እና ከኢትዮጵያ የስደተኞች እና ተመላሾች አገልግሎት ጋራ በመተባበር ችግሮቻቸውን ለመፍታት ባደረገው ጥረት ነው እስረኞችን ማስፈታቱን የገለጸው፡፡
ከእስር ተፈተዋል ያላቸው ስደተኞች፣ ከየትኛው ሀገር የመጡ እና ለምን ያኽል ጊዜ የታሰሩ እንደኾኑ ግን ሪፖርቱ አልጠቀሰም፡፡
በዚህ እና ተያያዥ ጉዳይ ላይ ማብራሪያ ለማግኘት በኢሜይል ለላክንለት ጥያቄ ዩኤንኤችሲአር ምላሽ እንደሚሰጠን ቢገልጽም፣ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ምላሹ አልደረሰንም፡፡ ከስደተኞች እና ተመላሾች አገልግሎት ማብራሪያ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ሊሳካልን አልቻለም፡፡
የስደተኞችን ጉዳይ በቅርበት ከሚከታተሉ ተቋማት አንዱ የኾነው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን(ኢሰመኮ) በበኩሉ፣ በኢትዮጵያ ቁጥራቸው በከፍተኛ መጠን እየጨመረ የሚገኙ ስደተኞች ለተለያዩ ችግሮች እየተጋለጡ እንደኾነ ገልጿል፡፡
የኢሰመኮ ተጠባባቂ ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ በሰጡን አስተያየት፣ በአብዛኛው ተመዝግበው እውቅና ማግኘት አለመቻል፣ የችግሮቹ መንሥኤ እንደኾነ ጠቅሰው፣ ይህም በተለይ የከተማ ስደተኞችን ለእስር እና መሰል ችግሮች ማጋለጡን ተናግረዋል፡፡ ኮሚሽኑም ከ120 በላይ እስረኞችን እንዳስለቀቀ አብራርተዋል፡፡
በከተማ ውስጥ ከሚኖሩ ስደተኞች መካከል የሚበዙት ኤርትራውያን እንደኾኑና በብዛት ለእስርም ተጋላጭ የኾኑት እነርሱ መኾናቸውን ወሮ. ራኬብ መሰለ ገልጸዋል፡፡ ዩኤንኤችሲአር “በሐምሌ ወር አስፈትቻቸኋለኹ” ስላላቸው እስረኞች ላነሣንላቸው ጥያቄም ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
በዐዲስ አበባ፣ በዓለምዋጭ እና በጾሬ፣ ከሐምሌ ወር ጀምሮ ከ7ሺሕ426 በላይ ስደተኞች “ፋይዳ” ዲጂታል መታወቂያ ካርድ እንደተሰጣቸው ዩኤንኤቺሲአር ገልጿል፡፡ በዐማራ ክልል እና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች የምዝገባ ማረጋገጫ የተሰጣቸው ስለመኖራቸውም በሪፖርቱ ጠቅሷል፡፡
የኢሰመኮ ተጠባባቂ ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ፣ የምዝገባው ሒደት በዋናነት በመጠለያ ካምፖች የተወሰነ መኾኑ፣ በተለይ በከተሞች የተመዝጋቢ ስደተኞች ቁጥር አነስተኛ እንዲኾን እና ለችግር እንዲጋለጡ ምክንያት መኾኑን አስረድተዋል፡፡
ከስደተኞች ምዝገባ ጋራ በተያያዘ ያሉ ችግሮች፣ በውይይት መፍትሔ ማግኘት እንዳለባቸውም መክረዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ፣ ከ1ነጥብ2 ሚሊዮን በላይ ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ይኖራሉ ተብሎ እንደሚገመት ተጠባባቂ ዋና ኮሚሽነሯ ተናግረዋል፡፡
እነዚኽ ስደተኞች በሦስት አማራጮች ማለትም፡ በኢትዮጵያ ከማኅበረሰቡ ጋራ ተቀላቅለው በመኖር፣ አሊያም ወደመጡበት ሀገር በመመለስ ወይም ወደ ሦስተኛ ሀገር በመሔድ ዘላቂ መፍትሔ ማግኘት የሚጠበቅባቸው ቢኾንም፤ ለሦስቱም አማራጮች ያለው ዕድል ጠባብ መኾኑ፣ ከካምፖች በመውጣት ወደ ከተሞች ገብተው መኖርን ምርጫቸው እንደሚያደርጉ የኢሰመኮ ተጠባባቂ ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ አብራርተዋል፡፡
ይህም የከተማ ስደተኞች ቁጥር እንዲጨምር ማድረጉን ጠቅሰው፣ በዐዲስ አበባ ከተማ ብቻ ከ80ሺሕ በላይ ስደተኞች እንደሚኖሩ ግምታቸውን አስቀምጠዋል፡፡
መድረክ / ፎረም