ዋሺንግተን ዲሲ —
በትግራይ ክልል ያለው የጸጥታ ሁኔታ አሁንም የተወሳሰበ እጅግ ያልተረጋጋ መሆኑን የሰብዓዊ ረድዔት ባልደረቦቻችን አሳውቀውናል ሲል ተመድ ገለፀ።
የተመድ ቃል አቀባይ በትናንት ዕለታዊ መግለጫቸው በትግራይ ክልል ያለው የጸጥታ ሁኔታ አሁንም የተወሳሰበ እጅግ ያልተረጋጋ መሆኑን የሰብዓዊ ረድዔት ባልደረቦቻችን አሳውቀውናል ብለዋል።
በዋና ዋና መንገዶች ጭምር ውጊያ እየተካሄደ መሆኑን በበርካታ አካባቢዎች የከባድ መሳሪያ ተኩስ መኖሩን ሪፖርቶች ደርሰውናል ያሉት የመንግሥታቱ ድርጅት ቃል አቀባይ ሴተፈን ዱጃሪች የዕርዳታ ድርጅቶች በተለይ ለመግባት አስቸጋሪ በሆኑ አካባቢዎች የህክምና አቅርቦት፣ ምግብ እና ሌላም ቁሳቁስ ለማድረስ መግባት የተከለከለ በመሆኑ አሁንም ችግር ላይ እንዳሉ ገልጸውልናል ብለዋል።
የረዳት ሰራተኞች ባልተገደበ እና ቀጣይነት ባለው መንገድ ተረጂውችን እንዲደርሱ እንዲፈቀድ እና ለርዳታ የሚውል ተጨማሪ ገንዘብም እንዲመደብ መጠየቃችንን እንቀጥላለን ብለዋል።
የተመዱ ቃል አቀባይ በዚሁ በትናንትናው ገለጻቸው "የቶጎጋ ከተማ የቦምብ ጥቃት በሚመለከት ከተማዋ ለመግባት ፈቃድ ስላላገኘን በስፍራው መገኘት አልቻልንም" ሲሉ መልሰዋል። የትናንት ዕለታዊ ገለጻቸው ነው፤ ከዚያ ወዲህ የተለወጠ ነገር ካለ መረጃ አላገኘንም።