በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የሚሌንየሙ የልማት ግቦች አካሄድ በየሃገራቸው አበረታች መሆኑን ኢትዮጵያና ኤርትራ አስታወቁ፡፡


140 መሪዎች የተገኙበት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዘንድሮ ጠቅላላ ጉባዔ ለሚሌኒየሙ የልማት ግቦች አያያዝ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየመከረ ነው፡፡

የሚሌኒየሙን የልማት ግቦች በተያዘላቸው ጊዜ ለመምታት እየተንቀሣቀሱ መሆናቸውን ኢትዮጵያና ኤርትራ አስታወቁ፡፡

ኒውዮርክ ላይ በመካሄድ ላይ ባለው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ትናንት ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ዓለምአቀፉ ቃል እየሄደ ያለበት ፍጥነትና ጥራት አምስት ዓመታት ብቻ የቀሩትን የሚሌኒየሙን የልማት ግቦች መምታት ይቻል እንደሆነ ግልፅ ማረጋገጫ መስጠት እንደማይቻል አመልክተዋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ የሚሌኒየሙን የልማት ግቦች በመንግሥታቱ ድርጅት ሥርዓት ውስጥ አንድነትን በመፍጠር ተመሣሣይ የሌላቸው መሆኑን የጠቆሙት የኤርትራው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦስማን ሣለህ ግቦቹን የመምታት ጉዳይ አሁንም ቅድሚያ ተሰጥቶት ሊቀጥል የሚገባው መሆኑን አሣስበዋል፡፡

የዘንድሮው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየተነጋገረ ያለው ድህነትን፣ ረሃብና በሽታዎችን ከዓለም በማስወገድ አጀንዳ ላይ ሲሆን ሊጠናቀቅ አምስት ዓመታት ብቻ የሚሌኒየሙ የልማት ግቦች ዕቅድ አካሄድን እየገመገመ ይገኛል፡፡

በጉባዔው ላይ የተገኙት የመንግሥታት መሪዎች እና ተጠሪዎቻቸው የየሃገራቸውን የልማት ግቦቹን አካሄድ የሚገመግሙ ንግግሮችና ሪፖርቶችን አቅርበዋል፡፡

በጉባዔው ላይ የኢትዮጵያን ግምገማ ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ሃገራቸው ግቦቹን ለመምታት አበረታች በሆነ መንገድ ላይ የምትገኝ መሆኑን ጠቁመው ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ ቃሉን እንዲያጠናክርና ቁርጠኝነቱንም በድጋሚ እንዲያረጋግጥ ጠይቀዋል፡፡

የኤርትራን ሪፖርት ያቀረቡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ አቶ ኦስማን ሣለህም ሃገራቸው የሚሌንየሙን የልማት ግቦች በ2015 ለመምታት የተቻላትን ሁሉ ለማድረግ መቁረጧን ተናግረዋል፡፡

"ረሃብን ያለፈ ታሪክ ለማድረግም በተለይ በመሠረተ-ልማትና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር አፍስሣለች" ብለዋል፡፡

በያዝነው ሦስተኛው ሚሌኒየም መባቻ ላይ እስከ 2015 ዓ.ም ድረስ መከናወን አለባቸው ብሎ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በ2000 ዓ.ም ያፀደቃቸው ስምንቱ ግቦች፡-

- የበረታ ድህነትና ረሃብን ማስወገድ፤

- የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርትን ለሁሉም ማዳረስ፤

- የፆታ እኩልነትን ማራመድ እና የሴቶችን አቅም ማጎልበት፤

- የሕፃናትን ሞት መጠን መቀነስ፤

- የእናቶችን ጤና ማሻሻል፤

- ኤችአይቪ/ኤድስን፣ ወባንና ሌሎችም በሽታዎችን መዋጋት፤

- የተፈጥሮ አካባቢን ደህንነት ማረጋገጥ፤

- ለልማት ዓለምአቀፍ አጋርነትን ማጠናከር ናቸው፡፡

የእነዚህን ግቦች ያለፉ አሥር ዓመታት ጉዞ በሚገመግመው በዘንድሮው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ 140 የሚሆኑ መሪዎች ተገኝተዋል፡፡

ለዝርዝሩ ዘገባውን ያድምጡ፡፡

XS
SM
MD
LG