በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ዩክሬን በተመድ ጠንካራ ድጋፍ አገኘች


የዩክሬን የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ዲሚትሮ ኩሌይባ
የዩክሬን የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ዲሚትሮ ኩሌይባ

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ በዩክሬን በድርጅቱ ቻርተር መርሆች መሰረት "በአፋጣኝ አጠቃላይ፣ ፍትሀዊ እና ዘላቂ ሰላም እንዲመሰረት" የሚጠይቀውን ውሳኔ ትናንት ሐሙስ በከፍተኛ ድምጽ ደግፏል።

ዩክሬን ያስገባችውን እና የሰላሙን አስፈላጊነት አበክሮ የሚያስገነዝበውን ውሳኔ 141 ሀገሮች ሲደግፉት ኤርትራን ጨምሮ ሰባት ሀገሮች ሲቃወሙት ኢትዮጵያን እና ቻይናን ጨምሮ 32 ሀገሮች ድምጸ ተአቅቦ አድርገዋል።

ውሳኔው ሩሲያ ያለአንዳች ቅድመ ሁኔታ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚታወቀው የዩክሬን ግዛት ወታደሮቿን በሙሉ ባስቸኳይ እንድታስወጣ እና ውጊያው እንዲቆም ይጠይቃል።

የዩክሬን የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ዲሚትሮ ኩሌይባ በውሳኔው ላይ ድምጽ ከተሰጠ በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጡት ቃል "ዩክሬንን የሚደግፉት ምዕራባውያን ሀገሮች ብቻ አለመሆናቸውን ሰፊ ድጋፍ እንዳለን እና ይህ ድጋፍ እየቀጠለ እና እየተጠናከረ እንደሚሄድ የዛሬው ውሳኔ ተጨማሪ ማሳያ ነው" ብለዋል።

ሩሲያ ዩክሬን ላይ የከፈተችውን ጦርነት አንደኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ረቡዕ የተጠራው የመንግሥታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ አስቸኳይ ስብሰባ ትናንት በቀረበው ውሳኔ ላይ ድምጽ ሰጥቷል።

በጠቅላላ ጉባዔው ክርክር ላይ ንግግር ያደረጉት የዩክሬን የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ኩሌይባ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ከሀገራቸው ጎን እንዲቆም ተማጽነዋል። "የተመድ ቻርተር ሀገሮች በሉዓላዊነታቸው እና በግዛት አንድነታቸው እኩል መሆናቸውን የሚገልጽ መርኃ አለው። በመሆኑም ሰላማዊ መፍትሄ ለመፈለግ መሰረት ሊሆን እንደሚገባ በግልጽ ጠንካራ መልዕክት ማስተላለፍ ይገባል" ብለዋል።

በመንግሥታቱ ድርጅት የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድ የድምጽ አሰጣጡን ውጤት ተከትሎ ሲናገሩ" እነሆ ዛሬ ተስፋ እንደማንቆርጥ አሳይተናል። በአስቸኳይ ሰላም እንዲሰፍን ያስፈልጋል። ያን ዕውን ለማድረግ ዲፕሎማሲ እና ውይይት ባላቸው አቅም ላይም ተስፋ አንቆርጥም።

ለጠቅላላ ጉባኤው በቀረበው ውሳኔ ላይ በተካሄደው ክርክር ሩሲያን ጨምሮ ሰባ አምስት ሀገሮች ተሳትፈዋል።

የቀረበው ውሳኔ ፍሬ ቢስ እና ከዕውነታው የራቀ ነው ያሉት በድርጅቱ የሩሲያ አምባሳደር ቫሲሊ ኔቤንዚያ ሀገሮች እንዲቃወሙት ተማጽነዋል። የሞስኮ ደጋፊዋ ቤላሩስ ሁለት ማሻሻያዎችን ያቀረበች ሲሆን ሁለቱም ውድቅ ተደርገውባታል።

"ሩሲያ ጸረ ሰላም አይደለችም" ብለው አጥብቀው የተከራከሩት አምባሳደሯ "በዲፕሎማሲ ዘላቂ መፍትሄ ለመፈለግ ዝግጁ መሆናችንን በተደጋጋሚ አሳውቀናል። ጠላቶቻችን ግን ባለኒውክሊየር ኃያል እናሸንፋለን ከሚለው ከንቱ ቅዠታቸው ለመላቀቅ አልቻሉም " ብለዋል።

XS
SM
MD
LG