አንድ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሚደገፍ ፍ/ቤት፣ የቀድሞው የማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ፕሬዝደንት ፍራንሷ ቦዚዜ ላይ የመያዣ ትዕዛዝ ማውጣቱን አስታውቋል። ማዘዣው የወጣው ሠራዊታቸው ከእ.አ.አ 2009 እስከ 2013 ባለው ጊዜ ውስጥ በሰብዓዊነት ላይ ወንጀል ሳይፈፅም አልቀረም በሚል ነው።
በመዲናዋ ባንጊ ላይ የተሰየመውና ከሃገር ውጪ ካሉ ፍርድ ቤቶች ጋራ የሚሠራው ልዩ የወንጀል ችሎት፤ ቦዚዜ ግድያ፣ አስገድዶ መሰወር፣ ሰቆቃ፣ መድፈር፣ እና ሌሎችንም ኢሰብዓዊ ድርጊቶችን ፈፅመዋል ሲል ከሷል።
የ77 ዓመቱ ቦዚዜ በመፈንቅለ መንግስት ወደ ሥልጣን የመጡት በእ.አ.አ 2003 ሲሆን፣ ከአስር ዓመታት በኋላ ከወንበራቸው ተወግደዋል።
ቦዚዜ ካለፈው ዓመት መጋቢት ጀምሮ በስደት ጊኒ ቢሳዉ የሚገኙ ሲሆን፣ ከዛ ሆነው ዋናውን አማጺ ቡድን በመምራት ላይ ይገኛሉ።
በእ.አ.አ 2015 በተመድ እገዛ የተቋቋመው ችሎት ትዕዛዙን ያወጣው ባለፈው የካቲት መሆኑን እና ጊኒ ቢሳዉ ተጠርጣሪውን ቦዚዜ ይዛ እንድታስረክብ ጠይቋል።
ችሎቱ በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ተፈጽመዋል የሚባሉ የጦር ወንጀሎችን እንዲመረምር የተቋቋመ ነው።
መድረክ / ፎረም