በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ተመድ በየመን በተደጋጋሚ የሚከሰተው ጦርነት ማቆሚያ እንዲበጅለት ጠየቀ


ፎቶ ፋይል፦ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የየመን ልዩ መልዕክተኛ ሃንስ ግሩንድበርግ
ፎቶ ፋይል፦ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የየመን ልዩ መልዕክተኛ ሃንስ ግሩንድበርግ

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የየመን ልዩ መልዕክተኛ፣ በተለይም በቅርብ ጊዜ የሁቲ አማፅያን በቀይ ባህር መርከቦች ላይ ያደረሱትን ጥቃት በመጥቀስ፣ በሀገሪቱ እየተደጋገመ የሚከሰተውን ጦርነት ለማስቆም አፋጣኝ እርምጃ እንዲወሰድ ትናንት ረቡዕ ጠየቁ።

የየመን ሁቲ አማፅያን በጋዛ ለሚገኙ ፍልስጤማውያን አጋርነታቸውን ለማሳየት በሚል በመርከቦች ላይ ጥቃት ማድረሳቸው፣ ከዩናይትድ ስቴትስና እና ከእንግሊዝ የአየር ጥቃት ምላሽ እንዲሰጥ አድርጓል።

የመንግሥታቱ ድርጅት የየመን ልዩ መልዕክተኛ ሃንስ ግሩንድበርግ “በየመን የሚደረገው የሽምግልና ጥረት እንዳይሰናከል፣ በአገሪቱም ሆነ በአካባቢው ያሉ ተዋንያን የቀይ ባህር ሁኔታ እንዳይባባስ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ላይ እንዲሳተፉ እያደረግኩ ነው ሲሉ” ለፀጥታው ምክር ቤት ተናግረዋል።

ግሩንድበርግ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን ውጥረት ለመግታት በአስቸኳይ ተግባራዊ መደረግ አለባቸው ያሏቸውን ሶስት እርምጃዎች፤ ማለትም፣ ክልላዊ መረጋጋትን መፍጠር፣ ወታደራዊ ጥቃትን ማስወገድ እና ወደ ድርድር የሚደረገውን ሂደት በጥንቃቄ መጠበቅ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ምንም እንኳን በቅርቡ በተሞከሩ ሰላማዊ ድርድሮች የታዩ ለውጦች መኖራቸው ቢነገርም፣ የሁቲ አማጽያኑ የሚያደርሱት ጥቃት እና ምዕራባውያንም የሚሰጡት የአጸፋ ምላሽ የሰላም ጥረቱን አደጋ ላይ የጣለው መሆኑ ተመልክቷል።

ይህም ሆኖ ከሁሉም ተሳታፊ አካላት ለሰላም ፍላጎት እንዳላቸው የሚያመለክቱ የቅርብ ጊዜ ማረጋገጫዎችን ማየታቸውን ግሩንድበርግ ገልጸዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ ዕርዳታ ማስተባቢሪያ ቢሮ (ኦቻ) እንደዘገበው፣ ከየመኑ ግጭት ጋር በተያያዘ፣ በበሽታ እና የተመጣጠነ ምግብ ዕጦት ምክንያት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ህይወት ተቀጥፏል።

ከ18 ሚሊዮን በላይ የሚደርሱ የመናዊያን አጣዳፊ ዕርዳታ እንደሚፈልጉም ኦቻ ጨምሮ ገልጿል፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG