መፈናቀልና ጠኔ እየከፋ በመሆኑ አንድ ሦስተኛ የሚሆነው የሱዳን ሕዝብ በያዝነው ዓመት ሰብዓዊ ዕርዳታ ይሻል ሲል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታውቀ፡፡
በምግብ ዕጥረት የተጎዱ ሰዎች ቁጥር ለተከታታይ ሦስተኛ ዓመት ጨምሮ ታይቷል ሲል በተመድ የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (ኦቻ) ትናንት ያወጣው ሪፖርት አመልክቷል፡፡
ከአምስት ዓመት ዕድሜ በታች ያሉ አራት ሚሊዮን ሕጻናት እንዲሁም ነፍሰጡርና አጥቢ እናቶች ለጉዳት ከተጋለጡት ግንባር ቀደሙ ናቸው ያለው የኦቻ ሪፖርት፣ ሕይወት አድን ተመጣጣኝ ምግብ በዚህ ዓመት ያስፈልጋቸዋል ሲል አሳስቧል፡፡
ከሁለት ዓመታት በፊት የተፈጸመውን ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ተከትሎ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ዕርዳታ በመቋረጡ ቀድሞውንም በረድኤት ድርጅቶች እገዛ ስታዘግም የነበረችው ሱዳን ችግር ውስጥ ወድቃለች፡፡
15.8 ሚሊዮን የሚሆነው ወይም ከሶስት እጅ አንዱ የሚሆነው የሱዳን ሕዝብ በዚህ ዓመት ሰብዓዊ ዕርዳታ እንደሚሻና ቁጥሩም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ1.5 ሚሊዮን መጨመሩን ቢሮው አስታውቋል፡፡
በሃገሪቱ ያለው የሕክምናና የውሃ አቅርቦት አሳሳቢ ነው መባሉንም የኤኤፍፒ ዘገባ አመልክቷል፡፡