በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በትግራይ ያሉ ረድኤት ሠራተኞች ዝውውር መልሶ ቀጥሏል


የተመድ ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱጃሪች
የተመድ ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱጃሪች

በትግራይ ያሉ የረድኤት ሠራተኞች ዝውውር መቀጠሉን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ትናንት አስታውቋል።

ካለፈው ነሃሴ ወር ወዲህ ተቋርጦ የነበረው የረድኤት ሠራተኞቹ ዝውውር ትናንት መጀመሩንና፣ በአፋር በኩል በትናንትናው ዕለት በሰላም መውጣታቸውን የሰብዓዊ ድርጅት አጋሮቻችን ነግረውናል ሲሉ የተመድ ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱጃሪች ለዜና ሰዎች ተናግረዋል።

ሌሎች ሠራተኞችንም በቀርቡ እናስወጣለን ብለን ተስፋ እናደርጋለን ብለዋል ቃል አቀባዩ።

ዱጃሪች በዕለታዊ ጋዜጣዊ መግለጫቸው እንዳሉት የረድኤት የሠራተኞቹን መንቀሳቀስ መቻል በመልካም ቢቀበሉትም፣ በምድርና በአየር የሚደረገው ህይወት አድን የዕርዳታ አቅርቦት እንዲቀጥል ሲሉ ጥሪ አድርገዋል።

የተመድ የሰብዓዊ አየር በረራ አገልግሎት ካለፈው ነሃሴ ጀምሮ መቋረጡን ያስታወሱት ቃል አቀባዩ፣ የዕርዳታ አቅርቦትና፣ እጅግ አስፈላጊ የሆነው የሥራ ማስኬጃ ገንዘብ ወደ ክልሉ እንዳይገባ አድርጓል ብለዋል።

በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ አሁንም አሳሳቢ ነው ያሉት ዱጃሪክ በትግራይ፣ በአፋርና በአማራ ክልሎች ሴቶችንና ሕጻናትን ጨምሮ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች በጦርነቱ ምክንያት መፈናቀላቸውን ተናግረዋል።

በተጨማሪም ጦርነቱ በሚካሄድባቸው ክልሎች ባሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩም ገልጸዋል።

በትግራይ በአብዛኛው ቦታ፣ በአማራና በአፋር በርካታ ቦታዎች እየተካሄደ ባለው ውጊያ ምክንያት ተደራሽ መሆን እንዳልቻሉ የሰብዓዊ ድርጅት አጋሮቻችን ነግረውናል ያሉት ዱጃሪች፣ ይህም ዕርዳታ ለሚጠብቁና ለተፈናቀሉ በሺህ ለሚቆጠሩ ሰዎች መድረስ እንዳይቻል አድርጓል ብለዋል።

የአቅርቦት እጥረትም ሆነ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢኖሩም የሰብዓዊ አጋሮቻችን በሦስቱ ክልሎች መድረስ በቻሉባቸው ቦታዎች ሥራቸውን በማከናወን ላይ ናቸው ብለዋል ቃል የመንግሥታቱ ድርጅት ቃል አቀባይ።

በትግራይ ከሰብዓዊ ዕርዳታ ክምችቱ ማከፋፈሉ እና መሠረታዊ ግልጋሎቶች መስጠቱ እንደቀጠለ ነው ብለዋል።

ከመስከረም 16/2015 ዓ.ም ጀምሮ 32 የተንቀሳቃሽ የጤናና የምግብ ማዕከላት በ58 የጤና አገልግሎት መስጪያ ጣቢያዎች ሥራቸውን በመሥራት ላይ ሲሆኑ ድንኳን፣ መተኛ ምንጣፍ፣ የወባ መከላከያ ጥቅሎችና ጄሪካኖች በሰሜን ምዕራብ ትግራይ ተከፋፍለዋል ብለዋል።

በአማራና በትግራይ ደግሞ፣ አዲስ ተፈናቃዮች፣ የምግብ፣ የውሃ፣ የአስቸኳይ ግዜ መጠለያና የጤና አገልግሎት በማግኘት ላይ መሆናቸው ታውቋል።

በሌላ በኩል፣ የተመድ ቃል አቀባይ ሶማሊያን በተመለከተ በዕለታዊ መግለጫቸው እንዳሉት፣ ዋና ጸሃፊው አንቶንዮ ጉቴሬዝ ከትናንት በስቲያ በአልሻባብ የተፈጸመውንና፣ ባለሥልጣናትን ጨምሮ በርካታ ሰዎች የተገደሉበትን ጥቃት አውግዘዋል።

ለሟቾቹ ቤተሰቦች መጽናናትን የተመኙት ጉቴሬዝ፣ ሰላማዊ መንግሥት ለመመሥረት ሶማሊያ ለምታደርገው ጥረት ተመድ ድጋፍ እንደሚያደርግ በድጋሚ ቃል ገብተዋል።

የማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክን በተመለከተ በተሰጠው መግለጫ ደግሞ፣ ሦስት የባንግላዴሽ ዜግነት ያላቸው የሰላም አስከባሪ አባላት፣ መኪናቸው በተጠመደ ፈንጂ በምሽት ሲጋይ ህይወታቸው ማለፉን ጁዳሪክ ተናገረው፣ አራተኛው ተጎጂ ሕክምና በማግኘት ላይ መሆኑን ጠቁመዋል።

ዋና ጸኃፊው በጉዳዩ ላይ ኦፊሴላዊ መግለጫ ይሠጣሉ ብለው እንደሚጠብቁ ቃል አቀባዩ ስቴፋን ጁዳሪክ ተናግረዋል።

XS
SM
MD
LG