በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በኢትዮጵያ ሕፃናት ከትጥቃዊ ግጭት ሊጠበቁ እንደሚገባ ተመድ አሳሰበ


 በኢትዮጵያ ሕፃናት ከትጥቃዊ ግጭት ሊጠበቁ እንደሚገባ ተመድ አሳሰበ
please wait

No media source currently available

0:00 0:01:54 0:00

በኢትዮጵያ ሕፃናት ከትጥቃዊ ግጭት ሊጠበቁ እንደሚገባ ተመድ አሳሰበ

በኢትዮጵያ፣ በትጥቅ የተደገፈ ግጭት ውስጥ የሚያልፉ ሕፃናት ደኅንነት ሊጠበቅ እንደሚገባ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሕፃናት እና የትጥቅ ግጭት ልዩ ተወካይ ቨርጅኒያ ጋምባ ተናገሩ።

ልዩ ተወካዩዋ ይህን የተናገሩት፣ ግጭትን በዘላቂነት ለማስቆም በተደረሰው የሰላም ስምምነት ዐውድ ውስጥ፣ የሕፃናትን ጥበቃ ለማጠናከር ስለሚቻልበት ኹኔታ፣ በኢትዮጵያ ለሁለት ቀናት ያደረጉትን ጉብኝት አጠናቀው ከተመለሱ በኋላ በሰጡት መግለጫ ነው።

“በኢትዮጵያ፣ ሁሉም ሕፃናት ከትጥቅ ግጭት ሊጠበቁ ይገባል፤” ሲሉ፣ ከኢትዮጵያ ጉብኝታቸው በኋላ መግለጫ የሰጡት፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሕፃናት እና የትጥቅ ግጭት ልዩ ተወካይ ቨርጅኒያ ጋምባ አሳሰቡ፡፡

ግጭት፣ በሕፃናት ልጆች ላይ የሚያሳድረው ተጽእኖ ገና ሙሉ በሙሉ ሊታወቅ እንዳልቻለ ያመለከቱት ልዩ ተወካዩዋ፣ ብዙ ቁጥር ያላቸው ክሦች አሁንም በመጣራት ላይ እንዳሉ ተናግረዋል፡፡

ይኹን እንጂ፣ ትጥቃዊ ግጭቱ በተደረገባቸው አካባቢዎች ባሉ ኃይሎች ተይዘው የሚገኙ ሕፃናት፣ ያለምንም ቅድመ ኹኔታ በአስቸኳይ እንዲፈቱና ከማኅበረሰቡ ጋራ ተመልሰው መቀላቀል የሚችሉበት ድጋፍ፣ የግድ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ እንደኾነ፣ ቨርጅኒያ ጋምባ አክለው አስገንዝበዋል።

ልዩ ተወካይዋ፣ በኢትዮጵያ ጉብኝታቸው፥ በግጭት ወቅት፣ በሕፃናት ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ፣ እንዲሁም ሕፃናትንና ጾታዊ ጉዳቶችን ለመቀነስ የሚያግዙ፣ የረጅም ጊዜ የመልሶ ማቋቋም መርሐ ግብሮችን በተሻለ ኹኔታ መደገፍ ስለሚቻልበት መንገድ፣ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት እና ባለሥልጣናት ጋራ መወያየታቸውን፣ ድርጅታቸው ባወጣው መግለጫ አትቷል።

በግጭት የተጎዱ ሕፃናትን ጥበቃ ለማጠናከር እና በእነርሱ ላይ የሚፈጸሙ ከባድ የመብቶችን ጥሰቶች ለመከላከል፣ መንግሥት ያለውን ፍላጎት እና ገንቢ ተሳትፎውን በደስታ እንደሚቀበሉት ልዩ ተወካዩዋ ገልጸዋል።

በቀጣይ፣ የሰላም ውይይቶች ላይ የሚሳተፉ ወገኖች ሁሉ፣ በሚነጋገሩባቸው ጉዳዮች ውስጥ፣ የሕፃናት ጥበቃ ድንጋጌዎችን እንዲያካትቱም አሳስበዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት፥ በብሔራዊ ደረጃ የትጥቅ ማስፈታት፣ የተበታተኑ ታጣቂዎችን ማሰባሰብ እና መልሶ ወደ ሰላማዊ ኑሮ የመቀላቀል መርሐ ግብሮችን መጀመሩን ልዩ ተወካይዋ አድንቀዋል፡፡

ከዚኽም ጋራ፣ ከጾታዊ ጥቃት የተረፉ ሰዎችን ጨምሮ አገልግሎቶችን ለማሻሻል የሚደረገው ጥረት፣ የማኅበራዊ ደኅንነት ባለሞያዎችን ማሠልጠን፣ የማኅበረ ሥነ ልቡናዊ የሕክምና ድጋፍ የሚሰጡት የስልክ መሥመሮችንና ደኅንነቱ የተጠበቀ የሪፖርት ማሠራጫዎችን ማቋቋም እና ብሔራዊ የሽግግር ፍትሕ ሒደትን መጀመር አስመልክቶ፣ በመንግሥት የተወሰዱ ርምጃዎችን፣ “የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለመደገፍ ዝግጁ ነው፤” ሲሉ፣ ልዩ ተወካይዋ፣ አጽንኦት ሰጥተው መናገራቸውን መግለጫው አመልክቷል፡፡

XS
SM
MD
LG