በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ተመድ ለኢትዮጵያ ሰብአዊ ርዳታ የሚውል 1 ቢሊዮን ዶላር ለማሰባሰብ አቅዷል


ፎቶ ፋይል፦ አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ
ፎቶ ፋይል፦ አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በግጭት ለምትታመሰው፣ በጎርፍ እና ድርቅ ለተጠቃችው ኢትዮጵያ የሚያስፈልገውን የሰብአዊ ርዳታ አቅርቦት ከፍ ለማድረግ 1 ቢሊዮን ዶላር ለማሰባሰብ ማቀዱን ዛሬ ማክሰኞ አስታወቀ።

ከኢትዮጵያ እና ከእንግሊዝ መንግሥታት ጋራ በመተባበር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጄኔቫ ላይ ያካሄደው የገንዘብ ማሰባሰብ ዘመቻ ለ15.5 ሚሊዮን ሰዎች የሚሆን የነብስ አድን ርዳታ እና ለተጨማሪ 10 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሰዎች የሚሰጠውን የምግብ ዕርዳታ መጠን ለማሳደግ የታለመ መሆኑ ተመልክቷል።

“የአስቸኳይ ርዳታ የሚጠይቁት ሁኔታዎች በድርቅ እና በጎርፍ እንዲሁም በግጭት እየተባባሱ የመጡ ናቸው” ሲል ተመድ አስታውቋል።

"ኤልኒኞ በሰሜናዊ የሃገሪቱ ክፍል በሚገኙ ደጋማ አካባቢዎች ያለውን ድርቅ በማባባሱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የውሃ አቅርቦት ዕጥረት፤ የግጦሽ ሳር እጦት እና የምርት መጠን ማሽቆልቆል ያስከተሏቸውን ፈተናዎች ለመቋቋም እየተጣጣሩ ነው" ብሏል።

በዚህ ዓመት በግጭቶች እና የአየር ንብረት ለውጥ ባስከተሏቸው ችግሮች የተነሳ ቁጥራቸው ከ21 ሚሊየን በላይ የሚደርሱ ሰዎች በኢትዮጵያ ሰብአዊ ርዳታ እንደሚፈልጉ የገለጸው ኦቻ፣ ከሐምሌ እስከ መስከረም ባሉት ወራት ቁጥራቸው 10 ነጥብ 8 ሚሊዮን የሚደርስ ሰዎች ለከፋ የምግብ ዋስትና ዕጥረት መጋለጣቸውንም ገልጿል።

በተያያዘ እንግሊዝ ለኢትዮጵያ የምትሰጠውን ርዳታ መጠን ለማሳደግ ተጨማሪ 100 ሚሊዮን ፓውንድ (124 ነጥብ 58 ሚሊዮን ዶላር) እንደምትሰጥ አስታውቃለች።

በብሪታኒያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የልማት እና የአፍሪካ ጉዳዮች ምክትል ሚኒስትር አንድሪው ሚሸል ሲናገሩ ለኢትዮጵያ ተጨማሪ ርዳታ ለመስጠት የተገባው ቃል የባህረ ሰላጤውን አገሮች ጨምሮ “ሌሎች ሃገራት እንዲሳተፉ ያበረታታል” የሚል እምነት እንዳደረባቸው ተናግረዋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG