በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

“በሱዳን ውጊያ ከ700ሺሕ በላይ ዜጎች ለተፈናቃይነት ተዳርገዋል” - ተ.መ.ድ


ግጭቱን ሸሽተው ደቡብ ሱዳን ሬንክ ካውንቲ የሚገኝ የስደተኞች ካምፕ የሚደርሱ ተፈናቃዮች
ግጭቱን ሸሽተው ደቡብ ሱዳን ሬንክ ካውንቲ የሚገኝ የስደተኞች ካምፕ የሚደርሱ ተፈናቃዮች

በሱዳን የጦር ሠራዊቱ እና የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ውጊያ ከተቀሰቀሰ ወዲህ፣ ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር ከ700 ሺሕ ማለፉን፣ የተባበሩት መንግሥታት የዓለም አቀፍ ፍልሰት ድርጅት አስታወቀ።

ድርጅቱ ይህን ያስታወቀው፣ ዛሬ ማክሰኞ በአወጣው ሪፖርቱ ነው፡፡ ባለፈው ሳምንት ከነበረው 334ሺሕ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ቁጥር የአሁኑ በዕጥፍ ይበልጣል። በአገር ውስጥ በውጊያው ምክንያት ከቀዬአቸው ከተፈናቀሉት በተጨማሪ፣ 100ሺሕ ሱዳናውያን ወደ ሌሎች ሀገራት መሰደዳቸውን ድርጅቱ አመልክቷል።

ዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት ሪፖርቱን ያወጣው፣ የሁለቱ ተፋላሚዎች ልዑካን የሳዑዲ አረቢያ ንግግር እየቀጠለ ባለበት በዚኽ ወቅት ነው፡፡

የሱዳን የጦር ኃይል እና የፈጥኖ ደራሽ ኃይል ተወካዮች፣ የሰብአዊ ርዳታ አቅርቦት መተላለፊያ መንገድ ማመቻቸትን በሚመለከት፣ ሳዑዲ አረቢያ ጅዳ ላይ የጀመሩት ንግግር፣ ትላንት ሰኞ ለሦስተኛ ቀን የቀጠለ ሲኾን፣ ድርድሩ ውጤት አምጥቶ ይኹን አይኹን ግን የተገኘ ፍንጭ የለም።

ተገናኝተን የምንነጋገረው፣ ለሰብአዊ ተራድኦው መሳለጥ ምቹ ኹኔታን መፍጠርን በሚመለከት ለመነጋገር እንጂ ውጊያ ስለማቆም ልንደራደር አይደለም፤”

ሁለቱም ወገኖች ከጅምሩ፣ “ተገናኝተን የምንነጋገረው፣ ለሰብአዊ ተራድኦው መሳለጥ ምቹ ኹኔታን መፍጠርን በሚመለከት ለመነጋገር እንጂ ውጊያ ስለማቆም ልንደራደር አይደለም፤” ብለው በአጽንዖት ሲናገሩ ቆይተዋል።

ባለፈው ቅዳሜ የተጀመረው ንግግር፣ የሰብአዊ ረድኤት ድርጅቶች በውጊያው ለቆሰሉ፣ ለተፈናቀሉ እና በረኀብ ላይ ለሚገኙ ሰዎች ርዳታ ማስገባት እንዲችሉ በማድረግ ላይ ያተኮረ መኾኑ ተገልጿል።

የሳዑዲ አረቢያ መንግሥት፣ ለሱዳን የ100 ሚሊዮን ዶላር ሰብአዊ ርዳታ እንደሚልክ ቃል ገብቷል።

ትላንት ሰኞም፣ በዋና ከተማዋ ካርቱም፣ የአየር ጥቃት እና ተኩስ እንደነበር፣ የዐይን እማኞች ለአሜሪካ ድምፅ ገልጸዋል።

በሌላ በኩል፣ ሱዳን ትሪቢዩን በእሑድ ዕትሙ እንደዘገበው፣ የጦር ሠራዊቱ ተደራዳሪዎች ሦስት ጥያቄዎችን አቅርበዋል። ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ፣ ያለምንም ቅድመ ኹኔታ ከካርቱም እንዲወጣ፣ ለሰብአዊ ርዳታ ሲባል ተኩስ አቁሙ እንዲቀጥልና ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በሁለት ዓመት ውስጥ ከመደበኛው የጦር ሠራዊት ጋራ እንዲቀላቀል የሚሉ ጥያቄዎች ማቅረቡን ጋዜጣው ዘግቧል፡፡ ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ጥያቄዎቹን ይቀበል እንደኾነ፣ በግልጽ የሚታወቅ ነገር እንደሌለ ሱዳን ትሪቢዩን አክሏል።

የአየር ጥቃቱ፣ ቦምቡ እና ተኩስ ቆሞ ከሀገሪቱ ለመውጣት የምንችልበት ኹኔታ እንደሚፈጠር ተስፋ አደርጋለኹ፤”

ሱዳናውያን፣ ጅዳ ላይ የቀጠለውን ድርድር፣ በተስፋም በጥርጣሬ ጉራማይሌ ስሜት እየተከታተሉት ናቸው። በጦርነቱ ምክንያት፣ ከካርቱም ሸሽተው በአልጄዚራ ክፍለ ግዛት የተጠለሉት ሱማያ ሙሳ፣ ለአሜሪካ ድምፅ በሰጡት ቃል፥ “የአየር ጥቃቱ፣ ቦምቡ እና ተኩስ ቆሞ ከሀገሪቱ ለመውጣት የምንችልበት ኹኔታ እንደሚፈጠር ተስፋ አደርጋለኹ፤” ብለዋል።

በተያያዘ ዜና፣ የሱዳን ቀይ ጨረቃ ማኅበር፣ ለ200ሺሕ ሱዳናውያን ርዳታ ለማቅረብ ይችል ዘንድ አስቸኳይ ድጋፍ እንዲደረግለት ተማጽኖ ማቅረቡን፣ የዓለም አቀፍ የቀይ መስቀል እና ቀይ ጨረቃ ማኅበራት ፌዴሬሽን አስታውቋል፡፡

XS
SM
MD
LG