የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታ ምክር ቤት ስድሥት ሕገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች ላይ ሊቢያ ጠረፍ ፍልሰተኞች ላይ የብዝበዛ አድራጎት በመፈፀም ወንጅሎ ዓለምቀፍ ማዕቀብ ወስኖባቸዋል።
ሁለቱ ኤርትራውያንና አራት ሊቢያውያን ከአፍሪካ ሃገሮች በሜዲቴራንያን ባህር አቋርጠው አውሮፓና ሌሎችም ሃገሮች ለመግባት የሚጓጉ ፍልሰተኞችን የሚበዘብዝ ቡድን እና ሚሊሺያዎች አደራጅተው የሚንቀሳቀሱ ናቸው።
ከትናንት ሃሙስ ጀምሮ ተግባራዊ የሆነው ዓለምቀፍ ማዕቀብ ሥድስቱ ሕገወጥ አዘዋዋሪዎች የባንክ ሂሳብ እንዳይንቀሳቀስ እና ዓለምቀፍ ዝውውር እንዳያደርጉ ይከለክላል።
የፀጥታው ምክር ቤት በጉልበት ሰዎችን በሕገወጥ መንገድ በሚያዘዋውሩ ቡድኖች ላይ ማዕቀብ ሲያውጅ ይህ የመጀመሪይ ጊዜ ነው።
ሊቢያ ውስጥ ሕገወጥ አዘዋዋሪዎች በአንድ የባሪያ ንግድ ገበያ ላይ አፍሪካውያን ፍልሰተኞችን በጨረታ ሲሸጡ ባለፈው ኅዳር ወር የተላለፈ የሲኤንኤን ቴሌቭዥን ስርጭት በፍልሰተኞች ላይ የሚፈፀመውን በደል አጉልቶ አሳይቷል።
ማዕቀብ የተደነገገባቸውን ሥድስቱን ሰዎች ዝርዝር ያቀረበችው የምክር ቤቱ አባል ኔዘርላንድስ መሆንዋ ታውቋል።
ሁለቱ ኤርትራውያን ፍትዊ አብደልራዛቅ እና ኢርሚያስ ግርማይ በብዙ አስር ሺዎች የተቆጠሩ የሚበዙት ከአፍሪካ ቀንድ የሚነሱ ፍልሰተኞችን እያሽሎኮለኩ ወደሊቢያ ጠረፍ፣ ከዚያም ወደአውሮፓና አሜሪካ የሚያሻግሩ መሆናቸው ተዘግቧል።
የፌስቡክ አስተያየት መስጫ