በኮንጎ የሚካሄደው ጦርነት 350 ሺህ የሚሆኑ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ሰዎችን ካለመጠለያ ማስቀረቱትን ያስታወቀው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ በምስራቃዊ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ያለው ኹኔታ በፍጥነት እያሽቆለቆለ ነው ብሏል።
ባለፈው ሳምንት የኮንጎን ትልቁን ምስራቃዊ ከተማ፣ ጎማን የተቆጣጠረው እና በሩዋንዳ የሚደገፈው የኤም 23 ታጣቂ ቡድን ወደ ደቡባዊ የሀገሪቱ ክፍል እየገፋ ሲሆን፣ ይህም በሺሕች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች በሚገኙበት ደቡባዊ ክፍል ሰፊ ሰብአዊ ቀውስ ሊፈጥር ይችላል ሲሉ የአካባቢው ባለሥልጣናት አስጠንቅቀዋል።
የመንግሥታቱ ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነር (ዩኤን ኤች ሲ አር) ቃል አቀባይ ኢዩጂን ቢዩን በጄኔቫ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉት 350 ሺሕ ሰዎች በጊዜያውነት ተጠልለውባቸው የነበሩት ካምፖች በመውደማቸው ምንም ዐይነት መጠለያ እንደሌላቸው ገልጸዋል።
በጎማ የሚገኙ 70 ከመቶ መጠለያ ጣቢያዎች ሙሉ ለሙሉ መውደማቸውን እና ሚኖቫ ውስጥ የሚገኙ ሌሎች መጠለያዎች ደግሞ ጉዳት እንደደረሰባቸውም አስረድተዋል።
በኮንጎ ወንጀል እና የበሽታ አደጋ መጨመሩንም ያመለከተው ኮሚሽኑ፣ ሌሎች ተቋማትም በግጭቱ ምክንያት ርዳታ ለማቅረብ መቸገራቸውን አብራርቷል።
ሩዋናዳ አማፂያኑን የኤም 23 ቡድን በወታደሮቿ እና በጦር መሳሪያ ድጋፍ ትሰጣለች በሚል ከኮንጎ እና ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ክስ የሚቀርብባት ሲኾን፣ ኪጋሊ በበኩሏ ክሱን አትቀበልም።
አሁን እንደአዲስ በተቀሰቀሰው ጦርነት ቢያንስ 3ሺሕ ሰዎች ህይወታቸው ያለፈ ሲሆን፣ በመቶ ሺሕዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል።
መድረክ / ፎረም