በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ቡሩንዲ ወደ ተስፋፋ ብጥብጥ ኣፋፍ ላይ ነች


የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታ ምክር ቤት አንድ ርምጃ እንዲወስድ አንድ ከፍተኛ የተ. መ.ድ. ጽ/ቤ ባለስልጣን ተማጽነዋል።

ቡሩንዲ ወደተስፋፋ ብጥብጥ አፋፍ ላይ ነች ሲሉ ኣንድ ከፍተኛ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባለስልጣን ኣስጠነቀቁ። የጸጥታ ምክር ቤቱ አንድ ርምጃ እንዲወስድም ተማጽነዋል።

የመንግሥታቱ ድርጅት ከፍተኛው የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽነር ትናንት ሰኞ ማታ ለምክር ቤቱ ባሰሙት ንግግር ቡሩንዲ ውስጥ ጸረ መንግሥት የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች ከጀመሩበት ካለፈው ሚያዝያ ወር ወዲህ ቢያንስ ሁለት መቶ ኣርባ ሰው መገደሉን ገልጸዋል። በእያንዳንዱ ሌሊት ኣስከሬኖች በየጎዳናው ኣስከሬኖች ተጥለው ማየት የተለመደ ሆኑዋል ሲሉ የተ መዱ ባለስልጣን ኣስረድተዋል።

ዘኢድ ራዓድ ኣል ሁሴን በንግግራቸው ቡሩንዲ ውስጥ ለሚደርሰው ለኣብዛኛው ጥቃት ተጠያቂዎቹ ፖሊሶች የመንግሥት የደህንነት ኣባላት እና ኢምቦኔራኩሬ የሚባሉት የገዢው ፓርቲ ሚሊሺያዎች ናቸው ብለዋል። ማንነታቸው የማይታወቅ የመንግሥት ተቃዋሚዎችም ግድያ እንደሚፈጽሙ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽነሩ ሳይገልጹ ኣላለፉም።

አሁን በሀገሪቱ ያለው ቀውስ የብሄረሰብ ግጭት መልክ ሊይዝ እንደሚችል ኣስረድተው የጸጥታው ምክር ቤት ካሁን ቀደም የነበሩትን የመሰሉ ዘግናኝ ብጥብጦች እንዳይደገሙ ይከላከል ዘንድ ተማጽነዋል።

እ ኤ አ በ2005 ዓመተ ምህረት ባበቃውና ለኣስራ ሁለት ዓመታት በተካሄደው የቡሩንዲ የርስ በርስ ብጥብጥ ወደሶስት መቶ ሺህ የሚገመት ህዝብ ተገድሎበታል። በኣጎራባች ሩዋንዳ በ1994 ዓመተ ምህረት በተካሄደው የዘር ማጥፋት ቢያንስ ስምንት መቶ ሺህ ህዝብ እንዳለቀ ኣይዘነጋም።

የተ መ ዱ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽነር በተማጽኖኣቸው የጸጥታው ምክር ቤት ኣሁን በቡሩንዲ ያለውን ቀውስ ለማስቆም ጥቃት እንዲካሄድ የሚቀሰቅሱ ወይም የሚካፈሉ ወገኖች ላይ ማዕቀብ መጣል፡ በድርጅቱ ቻርተር መሰረት ጦርነትን የማስቆም ርምጃዎች እንዲወስድ የሚፈቅደውን ኣንቀጽ ስራ ላይ ማዋልን ጨምሮ የተለያዩ ኣማራጮችን እንዲጠቀም ኣሳስበዋል።

የቡሩንዲ ፕሬዚደንት መሳሪያ ያላችሁ አስረክቡ ኣለዚያ በአገር ጠላትነት ትፈረጃላችሁ በማለት ማስጠንቀቂያ መስጠታቸውን ተከትሎ ባለፈው ሳምንት በርካታ ሰዎች ከመኖሪያቸው ሸሽተዋል።

የዩናይትድ ስቴትስ የኣፍሪካ ታላላቆቹ ሃይቆች አካባቢ ልዩ ልዑክ ቶማስ ፔሪዬሎ በቡሩንዲ የኣራት ቀናት ጉብኝት እያደረጉ ናቸው።

ልዩ ልዑኩ ዛሬ ማክሰኞ ባወጡት መግለጫ ለሳምንት ያህል ከግራ ከቀኝ ሲወረወሩ የነበሩት ጠብ አጫሪ ንግግሮች በሳምንቱ መጨረሻ ጋብ ማለታቸው ኣበረታቶናል ብለዋል።

አያይዘውም የሀገሪቱ የጦር ሰራዊት ገለልተኛ ሆኖ በመቆየቱ ኣመስግነው ሁለቱም መንግሥቱና ተተቃዋሚዎቹ ቀውሱ ፖለቲካዊ እንጂ ብሔረሰባዊ ኣለመሆኑን አረጋግተዋል ብለዋል።

ዝርዝሩን ከተያያዘው የድምጽ ፋይል በመጫን ያዳምጡ።

የተ.መ.ድ. ከፍተኛ ባለስልጣን፡ ቡሩንዲ ወደተስፋፋ ብጥብጥ ኣፋፍ ላይ ነች
please wait

No media source currently available

0:00 0:01:16 0:00

XS
SM
MD
LG