በሱዳን ከ16 ወራት በላይ በዘለቀው ጦርነት ከ20 ሺህ በላይ ሰዎች መሞታቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከፍተኛ ባለስልጣን ትላንት እሁድ አስታወቁ።
የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ቴድሮስ አድሃኖም ገብረ ኢየሱስ ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያለው በጦር ሠራዊቱ የሚደገፈው የሱዳን መንግሥት መቀመጫ በሆነችው ፖርት ሱዳን ከተማ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የሟቾች ቁጥር ከዚህ በላይ ሊሆን እንደሚችልም አመልክተዋል።
ቴድሮስ በሱዳን ያካሄዱትን የሁለት ቀናት ጉብኝት ባጠናቀቁበት ወቅት "ሱዳን አሰቃቂ በሆነ አጣዳፊ ሁኔታ ውስጥ ነች" ያሉ ሲሆን ግጭቱን ለመግታት እየተወሰደ ያለው እርምጃ በቂ አለመሆኑን አስምረውበታል።
በሱዳን እየተካሄደ ያለው ጦርነት በዓለም ላይ ትልቁን የመፈናቀል ቀውስ ያስከተለ ሲሆን ግጭቱ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ ከ13 ሚሊየን በላይ ሰዎች ቤት ንብረታቸውን ጥለው ለመሰደድ መገደዳቸውን የዓለም አቀፍ ፍልሰተኞች ድርጅት (IOM) መረጃ ያሳያል። ከነዚህ ውስጥ ከ2.3 ሚሊየን በላይ የሚሆኑት ወደ ጎረቤት ሀገራት መሰደዳቸውም ተመልክቷል።
በጦርነቱ ተሳታፊ የሆኑት ሁለቱም ወገኖች ግድያ፣ አካል ማጉደል እና ማሰቃየትን ጨምሮ በጦር ወንጀሎች መሳተፋቸውን የሚገልጹት በተባበሩት መንግስታትድ ድርጅት የሚደገፉ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መርማሪዎች በበኩላቸው፣ ሲቪሎችን ከጥቃት ለመጠበቅ "ገለልተኛ ኃይል" እንዲቋቋም ጠይቀዋል።
መድረክ / ፎረም