ሊቢያ ውስጥ ወደ 2.5 ቶን የሚገመት ዩራኒየም ከተከማቸበት መሰወሩን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኒውክለር ተቆጣጣሪ አካል አስታወቀ፡፡ ጦርነት በደቆሳት ሊቢያ ተሰውሯል የተባለው ዩኒራየም የደህንነትና ለጦር መሳሪያነት ሊውል ይችላል የሚል ሥጋት መፍጠሩን ተቆጣጣሪው አካል አስታውቋል፡፡
ጠፍቷል የተባለውና የብረት ዘር የሆነው የተፈጥሮ ማዕድኑ ዩራኒየም ገና ወደ ጋዝነት ያልተቀየረ በመሆኑ ለኃይል ምንጭ ወይም ለቦምብ ነዳጅ ወዲያውኑ የሚውል አለመሆኑን ባለሙያዎች መናገራቸውን አሶሴይትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
ይሁን እንጂ ቴክኖሎጂውና አቅሙ ያላቸው ዩራኒየሙን በማበልጸግ ወደ ሚፈለገው ደረጃ ሊያደርሱት ይችላሉ የሚል ሥጋት መፍጠሩ በዘገባው ተመልክቷል፡፡
መሰረቱን ቪያና ያደረገው ዓለም አቀፉ የአውቶሚክ ኤነርጂ ተቋም ዋና ዳይሬክተር ራፋኤል ማሪያኖ ግሮሲ ስለዩራኒየሙ መጥፋት ለአባል አገሮቹ ያስረዱት ትናንት ረቡዕ መሆኑ ተዘግቧል፡፡
የጠፋው ዩራኒየም የነበረው ከመንግሥት ቁጥጥር ውጭ በሆነ በተቃዋሚ አማጽያን ይዞታ ላይ እንደነበርም ሲገለጽ ተቆጣጣሪ አካሉም ተጨማሪ መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆኑን ተዘግቧል፡፡
የቀድሞ የሊቢያ መሪ ኮ/ል ሞአመር ጋዳፊ እኤአ ከ2003ቱ የዩናይትድ ስቴትስ መራሹ የኢራቅ ጦርነት በኋላ የኒውከለር ጦር መሳሪያ ባለቤት ለመሆኑ ፕሮግራማቸውን ይፋ ባደረጉበት ወቅት ወደ 1ሺ ሜትሪክ ቶን ዩራኒየም አከማችተው እንደነበር በዘገባው ተጠቅሷል፡፡
ዩራኒየሙ ከሊቢያ ዋና ከተማ ትሪፖሊ በስተደቡብ 660 ኬሜ ርቀት ላይ በምትገኘው የሳባህ ግዛት ውስጥ ሊገኝ ይችላል የሚል ግምት መኖሩም ተመልክቷል፡፡
ምንም እንኳ የተባበሩት መንግሥታት እኤአ በ2009 የበለጸገውን ዩንራኒየም ማስወገድ ቢችልም ቢጫ ዩራኒየም የተባለው ወደ ኋላ የተተወ በመሆኑ 6ሺ400 በርሜል የሚሆነው ሳባህ ውስጥ የተከማቸ መሆኑን እኤአ በ2013 አስታውቋል፡፡
ግዛቲቱ የሊቢያን መንግሥት ለመጣል በሚታገለውና በካሊፋ ኢፍጠር በሚመራው ጦር ቁጥጥር ስር መሆኗ ተነግሯል፡፡