በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በሱዳን ፍልሚያው በዳርፉር እና በካርቱም ቀጥሏል


የቃጠሎ ጭስ ካርቱም ሱዳን ሰማይ ላይ
የቃጠሎ ጭስ ካርቱም ሱዳን ሰማይ ላይ

በሁለቱ የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች መካከል የሚካሔደው ውጊያ፣ በምዕራብ የአገሪቱ ክፍል ዳርፉር እና በዋና መዲናዪቱ ካርቱም አይሎ መቀጠሉ ተነግሯል።

የአሜሪካ እና የሳዑዲ አረቢያ ታዛቢዎች፣ ሁለቱ ወገኖች፣ ለተኩስ ማቆሙ ያላቸው ዝንባሌ መሻሻል አሳይቷል፤ ቢሉም፣ ይጸናል የተባለው ተኩስ ማቆም ሳይዝለት አራት ቀናትን በውጊያ አሳልፏል።

በዋና መዲናዪቱ ካርቱም፣ የአየር ድብደባ እና የተኩስ ልውውጥ እንደነበር፣ የዓይን ምስክሮች መናገራቸውን፣ የኤኤፍፒ ዘገባ አመልክቷል።

አምስተኛ ሳምንቱን በአስቆጠረው ውጊያ፣ 1ሺሕ 800 ሰዎች እንደተገደሉና ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚኾኑቱ ደግሞ እንደተፈናቀሉ እየተነገረ ይገኛል።

ባለፈው ቅዳሜ፣ ጀዳ ላይ ስምምነት እንደተደረሰበትና ለአንድ ሳምንት እንደሚሰነብት የተነገረለት ተኩስ ማቆም፣ ቀደም ሲል እንደነበሩት ኹሉ ሳይተገበር ሲቀር፣ ለስምምነቱ ክሽፈት፣ አንዱ ሌላውን ወገን ተጠያቂ ያደርጋል።

አሜሪካ እና ሳዑዲ አረቢያ፣ ስምምነቱ መጣሱን፣ ከትላንት በስቲያ ረቡዕ አስታውቀዋል፡፡ ስምምነቱ ባለመተግበሩ አሜሪካ ማዕቀብ እንደምትጥል ብትዝትም፣ እስከ አሁን የትኛውም ወገን ላይ አልጣለችም።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ግጭቱ ከጀመረበት ሚያዝያ ሰባት ቀን ጀምሮ፣ 90 ሺሕ የሚኾኑ ሱዳናውያን፣ ወደ ጎረቤት ቻድ መሰደዳቸውን፣ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር አስታውቋል።

320ሺሕ የሚኾኑት ደግሞ ወደ ግብጽ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ቻድ፣ ኢትዮጵያ፣ ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ እንዲሁም ሊቢያ መሰደዳቸው ታውቋል።

XS
SM
MD
LG