የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የመን ጠረፍ ላይ ለብዙ ዓመታት ከቆመችው ነዳጅ ጫኝ መርከብ ነዳጁን በማውጣት የባሰ አደጋን የሚከላከል መርከብ ገዛ።
የመንግሥታቱ ድርጅት የልማት ፕሮግራም ዩኤንዲ ፒ ይህን ያልተለመደ የሆነ ግዢ መፈጸሙን ትናንት ያስታወቀ ሲሆን መርከቡ ነዳጁን ከቆመችው መርከብ ለመቅዳት በቅርቡ ወደየመን እንደሚጓዝ አመልክቷል።
ከተሰራች 47 ዓመት ያለፋት መርከብ እአአ በ2015 የየመን ጦርነት በተቀሰቀሰበት ወቅት በአማፂያን ከተያዘው ሁዲይዳ ወደብ ላይ ያልተንቀሳቀሰች ሲሆን ዕድሳት ተደርጎላትም አያውቅም።
የመንግሥታቱ ድርጅት መርከቡ ተገዝቶ እየበሰበሰች ካለችው መርከብ ላይ ድፍድፍ ነዳጁን እንዲያወጣ መደረጉ ሊደርስ የሚችለውን መጠነ ሰፊ የተፈጥሮ አካባቢ እና ሰብዓዊ አደጋ ለመከላከል የሚረዳ ትልቅ እርምጃ መሆኑን አመልክቷል።
አንድ ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ የጫነው መርከብ ቢፈራርስ እና ነዳጁ ቢፈስ ለማጽዳት ሃያ ቢሊዮን ዶላር ወጪ ሊተይቅ እንደሚችል የመንግሥታቱ ድርጅት ባለሥልጣናት ሲያስጠነቅቁ ቆይተዋል።