በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በመንግሥታቱ ድርጅት ተማጥኖ ለሱዳን የ1.5 ቢሊዮን ዶላር ርዳታ ተሰባሰበ


የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዥ
የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዥ

የሱዳንን ሕዝብ ለመርዳት በቅርቡ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በተላለፈ ጥሪ፣ 1.5 ቢሊዮን ዶላር መሰባሰቡን፣ የድርጅቱ ባለሥልጣናት፣ ትላንት ሰኞ አስታወቁ።

የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዥ፣ በቪዲዮ አማካይነት ባሰሙት ንግግር፣ “ሱዳን ወደ እልቂት እና ውድመት የወረደችበት ፍጥነት እና መጠን፣ ከዚኽ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ነው፤” ሲሉ፣ በመላ አገሪቱ በተደረጉ ግጭቶች፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ንጹሐን ዜጎች እንደተገደሉ ተናግረዋል።

ከሱዳን ግጭትም በፊት፣ አገሪቱ ቀድሞውንም፣ “በሰብአዊ ቀውስ እየተናጠች ነበር፤” ያሉት ዋና ጸሐፊ ጉተሬዥ፣ አሁን ደግሞ፣ “በእጅጉ እየተፋጠነና አሠቃቂ ውድመትን እያስከተለ ይገኛል፤” ብለዋል።

ጉተሬዥ አክለውም፣ “በጦርነት የተበታተከችውን አገር ሕዝብ መርዳት፣ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሓላፊነት ነው፤” ሲሉ አስረግጠው ተናግረዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ቮልከር ተርክ በበኩላቸው፣ “በዳርፉር የሚገኙትን 5ነጥብ6 ሚሊዮን ሰዎች ጨምሮ፣ ቁጥሩ ከ13 ሚሊዮን በላይ የሚልቅን ሕዝብ፣ አስቸኳይ የሕይወት አድን ሰብአዊ ድጋፍ በሚያስፈልግባት አገር ያለው ኹኔታ እጅግ የከፋ ነው፤” ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት፣ በከፍተኛ የምግብ እጥረት እየተሠቃየ ያለው ሕዝብ ቁጥር፣ 620ሺሕ ስለመድረሱም ተዘግቧል። “ዐዲስ የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት፣ ይህን የሥቃይ ውርጅብኝ ለመቀልበስ፣ ዐዲስ ዕድል ነው፤” ያሉት ኮሚሽነር ተርክ፣ “ሁለቱ ወገኖች፣ ዓለም አቀፍ የሰብአዊነት እና የሰብአዊ መብቶች ሕግጋትን የማክበር፣ የረድኤት ሠራተኞችንና ሌሎችንም ለመርዳት የተሠማሩ የሕክምና ባለሞያዎችን፣ ከማናቸውም አደጋ መከላከልን ጨምሮ፣ የሲቪሎችን ደኅንነት ለማስጠበቅ፣ አስፈላጊ ርምጃዎችን የመውሰድ ግዴታ እንዳለባቸው ለማስታወስ እወዳለኹ፤” ሲሉ አክለዋል።

XS
SM
MD
LG