በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ኔታንያሁ “የኦባማ አስተዳደር ከእሥራኤል ጀርባ ተመሣጥሯል” አሉ


የእሥራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ
የእሥራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ

እሥራኤል በኃይል በያዘችው የፍልስጥዔም ክልል ውስጥ የምታካሂዳቸውን የግንባታ ሥራዎች እንድታቆም በሚጠይቀው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት የውሣኔ ሃሣብ ላይ ዩናይትድ ስቴትስ ድምፅ ሳትሰጥ ቀርታለች፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ ድምፅ ከመስጠት መታቀብ የተቀሩት አሥራ አራት የምክር ቤቱ አባላት ውሣኔውን በሙሉ ድምፅ እንዲያሳልፉ አስችሏቸዋል፡፡

ውሣኔው በምክር ቤቱ ማለፉ እንደታወቀ የምክር ቤቱ ስብሰባ በጭብጨባ ተሞልቷል፡፡

የእሥራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ ፈጥነው በሰጡት ምላሽ ውሣኔውን “አሣፋሪና ፀረ-እሥራኤል እርምጃ” ሲሉ ያወገዙት ሲሆን ሃገራቸው ለውሣኔው እንደማትገዛ አስታውቀዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም “የኦባማ አስተዳደር እሥራኤልን ከዚህ ዓይነቱ የአፈና ተግባር አለመጠበቁ ብቻ ሳይሆን ከጀርባ ሆኖም ተመሣጥሯል” ብለዋል፡፡

“የዚህን ትርጉም የለሽ ውሣኔ ጎጂ ውጤቶች ለመቃረን እሥራኤል ከተመራጬ ፕሬዚዳንት ትራምፕ እና ወዳጆቻችን ከሆኑ የተወካዮች ምክር ቤቱ ሪፐብሊካንና ዴሞክራት እንደራሴዎች ጋር አብራ ትሠራለች” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ፡፡

ሃሣባቸውን ወዲያው በትዊተር ያሳወቁት ተመራጩ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እርሣቸው ሥራቸውን ሲጀምሩ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ ለውጥ እንደሚኖር ቃል ገብተው ቃለ-መሃላ ከሚፈፅሙበት የፊታችን ጥር 12 ብኋላ “ነገሮች ይቀየራሉ” ብለዋል፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጃን ኬሪ በሰጡት ቃል ውሣኔው ሁከትንና የአመፃ አድራጎቶችን እንዲሁም የሠፈራ እንቅስቃሴዎችን “ትክክለኛ” ባሉት ሁኔታ እንደሚያወግዝ ጠቁመው ሁለቱም ወገኖች አሁን ያለውን አዝማሚያ ለመቀልበስና የሁለት መንግሥታት መፍትኄን ዕውን ለማድረግ የሚያስችሉ ገንቢ እርምጃዎችን እንዲወስዱ አሳስበዋል፡፡

የፍልስጥዔም ተደራዳሪ ሳዔብ ኤሬካት በሰጡት መግለጫ “የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ድምፅ የኔታንያሁ ፖሊሲዎች ለእሥራኤልም ለአካባቢውም ሰላምና መረጋጋትን አንደማያመጣ የተለለፈ ግልፅ መልዕክት ነው” ብለዋል፡፡

እሥራኤል በኃይል በያዘቻቸው የፍልስጥዔም ክልል ላይ እያካሄደች ያለችውን የሠፈራ ግንባታ እንድታቆም የሚጠይቀውን የውሣኔ ሃሣብ ያቀረቡት ኒው ዚላንድ፣ ማሌዥያ፣ ሴኔጎል እና ቬኔዝዌላ ሲሆኑ የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤቱ ውሣኔውን ካሳለፈ በኋላ እሥራኤል ዲፕሎማሲያዊ እርምጃዎችን መውሰድ መጀመሯ ተገልጿል፡፡

የእሥራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ ሴኔጎል እና ኒው ዚላንድ ያሉ አምባሳደሮቻቸውን ለምክክር በሚል ወደ ቴል አቪቭ ጠርተዋል፡፡ ከማሌዥያና ከቬኔዝዌላ ጋር እሥራኤል ወትሮም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች አልነበሯትም፡፡

XS
SM
MD
LG