በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ እንደሚያሳስባቸው የተመድ ከፍተኛ ኮሚሽነር አስታወቁ


የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ዛይድ ራዓድ አል-ሁሴን(ግራ)እና በተመድ የጄኔቫ ቢሮ የኢትዮጵያ ቋሚ ተጠሪ አምባሳደር ነጋሽ ክብረት(ቀኝ)
የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ዛይድ ራዓድ አል-ሁሴን(ግራ)እና በተመድ የጄኔቫ ቢሮ የኢትዮጵያ ቋሚ ተጠሪ አምባሳደር ነጋሽ ክብረት(ቀኝ)

ኢትዮጵያ በተቃዋሚ ሰልፈኞች ላይ ታካሂደዋለች ያሉት ከመጠን ያለፈና ግድያ የታከለበት የኃይል አጠቃቀም በጥልቅ እንደሚያሳስባቸው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ዘይድ ራዓድ አል-ሁሴን ትናንት አሳስበዋል፡፡

የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ እንደሚያሳስባቸው የተመድ ከፍተኛ ኮሚሽነር አስታወቁ
please wait

No media source currently available

0:00 0:09:22 0:00

ኢትዮጵያ በተቃዋሚ ሰልፈኞች ላይ ታካሂደዋለች ያሉት ከመጠን ያለፈና ግድያ የታከለበት የኃይል አጠቃቀም በጥልቅ እንደሚያሳስባቸው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ዘይድ ራዓድ አል-ሁሴን ትናንት አሳስበዋል፡፡

ከፍተኛ በዚሁ ንግግራቸው “ኢትዮጵያ በምጣኔ ሃብት ዕድገት ጉልህ ውጤት ብታስመዘግብም ግድያን የጨመረ ከመጠን ያለፈ ኃይል በተቃዋሚ ሠልፈኞች ላይ እንደምትጠቀም፣ ሰዎች ደብዛቸው እንዲጠፋ እንደሚደረግ፣ ጅምላ እሥራቶች በሕፃናት ላይ ሳይቀር እንደሚካሄዱ፣ እንዲሁም በሲቪል ማኅበረሰብ፣ በመገናኛ ብዙኃንና በተቃዋሚዎች ላይ አፈና እንደምታካሂድ በተደጋጋሚ የሚቀርቡት ክሦች በጥልቅ ያሰስቡናል” ብለዋል፡፡

ቢሯቸው በተለይ ኦሮምያና አማራ ክልሎች ውስጥ የሰብዓዊ መብቶች አያያዞችን ቀርቦ እንዲመለከት ጥያቄ ማቅረባቸውን በዚሁ የትናንት ንግግራቸው የጠቆሙት ከፍተኛ ኮሚሽነር ዛይድ ራዓድ አል-ሁሴን በቅርቡ እየተስተዋሉ ያሉት ሁከቶች “በሕገወጦችና በሽብርተኛ ቡድኖች እየተካሄዱ ያሉ ናቸው” ተብሎ በመንግሥቱ እንደተነገራቸው አመልክተዋል፡፡

መንግሥት በሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ የተፈፀመውን ግድያ አስመልክቶ የራሱን ማጣራት እያደረገ መሆኑ የተነገራቸው ከፍተኛ ኮሚሽነር ዛይድ ራዓድ “ብሄራዊ ጥረቱን እደግፋለሁ፤ ይሁን እንጂ ክሦቹን ለማረጋገጥም ይሁን ውድቅ ለማድረግ መንግሥቱ ነፃ፣ ወገናዊ ያልሆኑና የዓለምአቀፍ ፍተሻዎችን አስፈላጊነት ግምት ውስጥ ማስገባት እንዳለበት አምናለሁ” ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከከፍተኛ ኮሚሽነሩ ጋር ካላት የተከበረ ግንኙነት በመነሣት የእርሳቸው ቢሮ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ ፍቃድ መነፈጉ እንደሚገርማቸው ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያ ላይ የተነሡት የሰብዓዊ መብቶች ረገጣ ክሦች መሠረተ-ቢስ ናቸው ሲሉ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጄኔቫ ቢሮ ቋሚ ተጠሪ አምባሣደር ነጋሽ ክብረት ዛሬ በሰጡት ምላሽ አስታውቀዋል፡፡

አምባሳደሩ በዚሁ ንግግራቸው ኦሮምያና አማራ ክልሎች ውስጥ እየታየ ያለውን ሁኔታ በቅርብ ለመያዝ የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍ ያለ ትኩረት የሰጠ መሆኑን ጠቁመው ከተቃውሞዎቹ ጋር ተያይዞ በሕይወትና በንብረት ላይ ለደረሱት ጉዳቶች ፌደራሉና የክልሉ መንግሥት ኀዘናቸውን ለተጎጂ ቤተሰቦች መግለፃቸውን፣ አስፈላጊ በሆኑ መንገዶች ሁሉ ለመርዳትም ዝግጁ መሆናቸውን ማሳወቃቸውን አመልክተዋል፡፡

ይሁን እንጂ “መንግሥቱ ሕግና ሥርዓትን ለማስከበር ፈጣን እርምጃ ባይወስድ ኖሮ ጉዳቶቹ የባሱ ይሆኑ ነበር” ያሉት አምባሳደር ነጋሽ ተቃውሞዎቹ በአንዳንድ የውጭና የሃገር ውስጥ የሁከት ባሏቸው አካላት ተጠልፈዋል ብለዋል፡፡

ባለፈው ሣምንት በኢትዮጵያ ላይ የአቤቱታ ደብዳቤ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ደብዳቤ ካስገቡ 15 ድርጅቶች መካከል አንዱ የሆነውና ሲቪከስ በሚል ምኅፃር የሚታወቀው የዓለም የዜጎች ተሣትፎ ጥምረት ተጠሪ ዛሬ በምክር ቤቱ ጉባዔ ላይ ባሰሙት ቃል የከፍተኛ ኮሚሽነሩን ሥጋት እንደሚደግፉ ተናግረዋል፡፡

የካናዳ ተጠሪም ሃገራቸው የሰብዓዊ መብቶች ረገጣዎች ያሳስቧታል ብላ ከምትጠራቸው ሃገሮች አንዷ ኢትዮጵያ መሆኗን ተናግረዋል፡፡

ለመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ባለስድስት ነጥብ ጥያቄ ያስገቡት መንግሥታዊ ያልሆኑት የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅቶች የኢትዮጵያ መንግሥት የፀጥታ ኃይሎቹ በኦሮምያና በአማራ ክልሎችና በሌሎችም አካባቢዎች የሚወስዷቸውን ከመጠን ያለፉና አስፈላጊ ያልሆኑ እስከ ግድያ የሚደርሱ እርምጃዎቻቸውን በአስቸኳይ እንዲያቆስቆም ጥሪ እንዲተላለፍለት መጠየቃቸው ተዘግቧል፡፡

የመብቶች ተሟጋች ድርጅቶቹ ካሠፈሯቸው ስድስት ጥያቄዎች መካከል መንግሥቱ በተቃውሞዎቹ ወቅትና ከዚያም በኋላ በዘፈቀደ ያሠራቸውን ጋዜጠኞች፣ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች፣ የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶች መሪዎችና አባላት፣ እንዲሁም በሰልፎች ላይ የተሣተፉትን ያለድርድርና በአፋጣኝ እንዲፈታ የሚል ይገኝበታል፡፡

በተጨማሪም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ልዩ ምርመራ ቡድኖች ወደ ሃገሪቱ እንዲገቡ ለቀረቡለት ጥያቄዎች መንግሥቱ አዎንታዊ መልስ እንዲሰጥ፣ እንዲሁም ዓለምአቀፍ የሆነ ጥልቀት ያለው ነፃና ከወገንተኝነት የፀዳ ግልፅ ምርመራ እንዲካሄድ ፈራሚዎቹ ድርጅቶች አሳስበዋል፡፡

በሃገሪቱ ውስጥ ለተፈፀሙ የሰብዓዊ መብቶች ረገጣዎች ተጠያቂ ናቸው የሚባሉ ዓለምአቀፍ ሕግጋትንና ደረጃዎችን በጠበቀ ሁኔታ እንዲጠየቁና በነፃ ፍትሕ እንዲዳኙ ማረጋገጫ እንዲሰጥ የሚሉ ጥያቄዎችም ተነስተዋል፡፡

ደብዳቤውን የፈረሙት አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር የሚሟገቱ ማኅበር፣ ሲቪከስ በሚል ምኅፃር የሚጠራው የዓለም የዜጎች ተሣትፎ ጥምረት፣ የሲቪል መብቶች ዘቦች፣ እንዲሁም ለዘቦች ዘብ ቁሙ የሚባለው ተቋም የምሥራቅ አፍሪካና የአፍሪካ ቀንድ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ፕሮጀክት፣ የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ፕሮጀክት፣ የሰብዓዊ መብቶች ዓለምአቀፍ ፌደሬሽን፣ የሰብዓዊ መብቶች ተነሣሽነት ድርጅት፣ ፍሪደም ሃውስ፣ የግንባር መስመር ተከላካዮች፣ የደኅንነት ጥበቃ ኃላፊነት ዓለምአቀፍ ድርጅት፣ ሂዩማን ራይትስ ዋች፣ የሰብዓዊ መብቶች ዓለምአቀፍ አገልግሎት፣ ድንበር የለሽ ሪፖርተሮች፣ የስቃይ አያያዝ ተቃዋሚ ዓለምአቀፍ ድርጅት ናቸው፡፡

ኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤቱ አባልና ምክትል ፕሬዚዳንት በመሆኗ የሰብዓዊ መብቶችን ጥበቃ ከፍተኛ ደረጃ ልታሟላ የሚጠበቅባት ሃገር መሆኗን የሚያስታውሰው ይህ ጥያቄ በመንግሥታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ውሣኔ 60/251፣ ኦፒ 9 መሠረት ሙሉ በሙሉ መተባበር እንደሚኖርባት ያሳስባል፡፡

ደብዳቤው በሃገሪቱ ውስጥ ተፈፅመዋል የሚላቸውን ግድያዎችና እሥራቶችም ቦታና ሁኔታ ይናገራል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ በተቃውሞዎች ወቅት ተፈፀሙ የተባሉ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን መንግሥቱ ሙሉ በሙሉ እንዲያጣራ ወይም ለአህጉራዊና ዓለማቀፋዊ ድርጅቶች ያልተገደበ የማጣራት ፈቃድ እንዲሰጥ የአፍሪቃ የሰብዓዊና የሕዝቦች መብቶች ኮሚሽን ላቀረበው ጥሪ የኢትዮጵያ መንግሥት በሰጠው ምላሽ አህጉራዊም ሆነ ዓለማቀፋዊ ቡድኖች እንደማይጋበዙ ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡

ሙሉውን ዘገባ ከላይ ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ያዳምጡ፡፡

ለተጨማሪ መረጃዎችና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት መክፈቻ ላይ ከፍተኛ ኮሚሽነር ዘይድ ራዓድ አል-ሁሴን ያደረጉትን ንግግር፤ በመንግሥታቱ ድርጅት የጄኔቫ ቢሮ የኢትዮጵያ ቋሚ ተጠሪ አምባሣደር ነጋሽ ክብረት ዛሬ የሰጡትን ምላሽ፤ እንዲሁም ሌሎቹን ንግግሮችን ማዳመጥ ከፈለጉ ከታች ያሉትን ማገናኛዎች ተጭነው ይከተሉ፡፡

http://webtv.un.org/meetings-events/human-rights-council/watch/zeid-ra%E2%80%99ad-al-hussein-item2-update-1st-meeting-33rd-regular-session-human-rights-council/5121905669001

http://webtv.un.org/meetings-events/watch/item2-general-debate-4th-meeting-33rd-regular-session-human-rights-council-/5121905721001

XS
SM
MD
LG