በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ጦር ኃይሎች የጦር ወንጀሎችን ሳይፈጽሙ አልቀሩም - ተመድ


ፎቶ ፋይል፦ የሱዳን ተፈናቃዮች ነዋሪዎች በዳርፉር፤ ሱዳን እአአ ሃምሌ 30/2020
ፎቶ ፋይል፦ የሱዳን ተፈናቃዮች ነዋሪዎች በዳርፉር፤ ሱዳን እአአ ሃምሌ 30/2020

በሱዳን ሥልጣን ለመያዝ የሚታገሉ ፈጥኖ ደራሽ ጦር ወታደራዊ ኃይሎች እና ሚሊሻዎቹ አጋሮቻቸው ምዕራብ ዳርፉርን ሲቆጣጠሩ ፈፅመዋቸዋል የተባሉት ዘርን የለየ መጠነ ሰፊ ግድያ እና መድፈር፣ የጦር እና በሰብአዊነት ላይ የተፈፀሙ ግድያዎች ሊኾኑ እንደሚችሉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባለሞያዎች ያወጡት አዲስ ሪፖርት አመለከተ።

ለመንግሥታቱ የፀጥታው ምክር ቤት የቀረበና ዛሬ ሐሙስ በአሶሽየትድ ፕሬስ እጅ የገባው ሪፖርት፣ አረቦች የሚበዙበት የፈጥኖ ደራሹ ጦር ኃይሎች፣ በዳርፉር አፍሪካውያን ላይ የፈጸሟቸው ዘግናኝ እና አሰቃቂ የጭካኔ ገጽታዎችን እንደሚያሳይ ተመልክቷል።

የፈጥኖ ደራሹ ጦር የተወሳሰቡ የፋያናንስ ተቋማትን መረብ መጠቀምን ጨምሮ ከአምስቱ የዳርፉር ግዛቶች አራቱን እንደምን አድርጎ በቁጥጥር ስር እንዳዋላቸው ዘገባው በዝርዝር ማስቀመጡም ተገልጿል፡፡

ሱዳን በጦር ሠራዊቱ አዛዥ በጄኔራል አብደል ፋታህ አል ቡርሃን እና በፈጥኖ ደራሹ መሪ መሐመድ ሃምዳን ዳጋሎ በሚመራው ጦር መካከል በተፈጠረ አለመግባባት ካለፈው ሚያዝያ ጀምሮ በከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ትገኛለች፡፡

ከካርቱም ጎዳናዎች የጀመረው ጦርነት ወደ ሌሎቹ በርካታ የሀገሪቱ አካባቢዎች መስፋፋቱ ሲነገር የዳርፉር ግዛት ግን ከሁሉም የተለየ መልክ መያዙ በዘገባው ተጠቅሷል፡፡

የፈጥኖ ደራሹ ጦር ኃይሎች በተለይም በአፍሪካውያኑ ማሳሊት በተባሉ ብሄረሰቦች ላይ የሚያደርሷቸው ጭካኔ የተሞላባቸው ጥቃቶች መበራከታቸው ተነግሯል፡፡

ለተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት የቀረበው ዘገባ ከአስርት ዓመታት በፊት ከፍተኛ የዘር ማጥፋት በተፈጸመባት ዳርፉር ከፍተኛ ጥፋት እየደረሰ ነው ይላል።

በዳርፉር ከአውሮፓውያን “ከ2005 ወዲህ እጅግ የከፋ ጥቃት” እየተፈጸመ መሆኑን የመንግሥታቱ ድርጅት ሪፖርት ጠቅሷል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG