በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ተመድ በሰሜን ኢትዮጵያ የሚያደርገውን ሰብአዊ ድጋፍ መቀጠሉን አስታወቀ


 የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ጸሐፊ ቃል አቀባይ ስቴፋን ጁዳሪክ
የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ጸሐፊ ቃል አቀባይ ስቴፋን ጁዳሪክ

በድጋሚ የታደሰ

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ መንግሥታዊ ካልኾኑ አጋሮቹ ጋራ በመተባበር፥ በአፋር፣ በአማራ እና በትግራይ የሚያከናውነውን ሰብአዊ ድጋፍ በማስፋፋት ላይ እንደኾነ አስታወቀ፡፡

ባለፈው ሳምንት መጨረሻ፣ በሰሜን ኢትዮጵያ ስለሚደረገው ሰብአዊ ድጋፍ፣ በኒውዮርክ ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡት የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ጸሐፊ ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱጃሪክ እንደተናገሩት፣ ካለፈው ጥቅምት ወር ጀምሮ፣ በትግራይ 4ነጥብ 7 ሚሊዮን፣ በአፋር እና በአማራ ክልሎች ደግሞ 2ነጥብ 5 ሚሊዮን የሚኾኑ ሰዎች የምግብ ርዳታ አግኝተዋል፡፡

11 ሚሊዮን የሚኾኑ ሰዎች በድርቅ በተጠቁበት በደቡብ እና በምሥራቅ የአገሪቱ ክፍሎች ደግሞ፣ ከመንግሥት ጋራ በመተባበር የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ ርዳታን እያፋጠኑ መኾኑን ዱጃሪክ ተናግረዋል፡፡

በሶማሌ ክልልም፣ ከድርቁ በተጨማሪ ጎርፍ፣ 230ሺሕ ሰዎችን ችግር ላይ መጣሉን፣ ቤቶች እና መሠረተ ልማቶች መፍረሳቸውን አመልክተው፣ በጎርፍ የተጠቁትን ማኅበረሰቦች ለመታደግ፣ የመንግሥታቱ ድርጅት ድጋፍ በማሰባሰብ ላይ እንደኾነ ዱጃሪክ አክለው ገልጸዋል፡፡

በኦሮሚያ እና በሶማሌ ክልሎች፣ የኮሌራ ወረርሽኝ በፍጥነት እየተዛመተ መኾኑንና ከጥር ወር ወዲህ 2ሺሕ300 ታማሚዎች መመዝገባቸውን፤ ይህም አኃዝ፣ በጥር ወር ከነበረው በእጥፍ መጨመሩን ያሳያል፤ ብለዋል፡፡ አያይዘውም፣ 51 ሰዎች በኮሌራ መሞታቸውን ባለሥልጣናት ማስታወቃቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በመላ አገሪቱ ለሚታየው ችግር ሰብአዊ ድጋፉን በአግባቡ ለማዳረስ፣ አራት ቢሊዮን ዶላር ያህል ተጨማሪ ገንዘብ እንደሚያስፈልግ ዱጃሪክ በመግለጫቸው አመልክተዋል፡፡ ይኹን እንጂ፣ እስከ አሁን የተገኘው፣ 727 ሚሊዮን ዶላር ወይም 18 በመቶው ብቻ እንደኾነ ገልጸዋል፡፡

XS
SM
MD
LG