የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታ ምክር ቤት አባላት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድና የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ባለፈው ሰኞ የሰላምና የወዳጅነት ሥምምነት መፈረማቸውን አሞግሰዋል ሲል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የወጣው መግለጫ አስታውቋል።
የፀጥታው ምክር ቤት አባላት አምስት ነጥቦችን ያቀፈ ዕቅድ መኖሩን ጠቅሰው ሁለቱም ወገኖች የኢትዮጵያና የኤርትራ ድንበር ኮሚሽን ውሳኔን ተግባራዊ ለማድረግ መስማምታቸውን በጥሩ መንፈስ ተቀብለውታል ይላል መግለጫው።
የፀጥታው ምክር ቤት አባላት ኤርትራና ኢትዮጵያ ተባብረው ክልላዊ ሰላም ለመጠበቅ፣ ለልማትና ለትብብር ያሳዩትን ቁርጠኛነት እናሞግሳለን። ኤርትራ በኢጋድ ማለት በምሥራቅ አፍሪካ የልማት ትብብር በይነ መንግሥታት ንቁ ተሳታፊ እንድትሆንም እንጠብቃለን ማለታቸውን መግለጫው ጠቅሷል።
የፀጥታው ምክር ቤት አባላት ኢትዮጵያና ኤርትራ የፈረሙትን ሥምምነት በመተግበር ለመርዳት ዝግጅ ነን ማለታቸውንም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መግለጫ ገልጿል።
የፌስቡክ አስተያየት መስጫ