የኤርትራ መንግሥት ለሩብ ምዕት ዓመት ያካሄደው የተስፋፋና የተደራጀ የሰብዓዊ መብቶች ረገጣ በሰብዕና ላይ የተፈፀሙ ወንጀሎችን ያህል ነው ሲል በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተቋቋመው የኤርትራ ሰብዓዊ መብቶች አያያዝ አጣሪ ኮሚሽን ከስሷል፡፡ ኮሚሽኑ ያወጣው ሪፖርት ዛሬ፤ ረቡዕ ሰኔ 1/2008 ዓ.ም ይፋ የተደረገው ጄኔቫ ላይ ነው፡፡
ኤርትራ “ነፃ የፍርድ ሥርዓት፤ ብሄራዊ ሸንጎ ወይም የተወካዮች ምክር ቤትና ዴሞክራሲያዊ ተቋማት የሌሉባት አምባገናዊ ግዛት ነች” ብለዋል የመንግሥታቱ ድርጅት የሰየማቸው የኤርትራ የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ አጣሪ ኮሚሽነሮች፡፡ “በሕዝቡ ውስጥ ፍርሃት ለማስረፅና የፖለቲካ ተቃውሞን ለመገደብ ሲባል የባርነት አያያዝ፤ እሥራት፣ ደብዛ ማጥፋትና ሌሎችም ኢሰብዓዊ ወንጀሎች ተፈፅመዋል” ብለዋል ኮሚሽነሮቹ፡፡
“በድብቅ ሥፍራዎች ውስጥ የሥቃይ አያያዝ፣ መድፈርና ግድያን የመሳሰሉ ረገጣዎች እንደሚካሄዱ፤ ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት ውስጥ በሃገሪቱ የብሄራዊ አገልግሎት ሥርዓት ውስጥ ዕድሜ ልካቸውን እንዲያገለግሉ የተበየነባቸው በግምት ከሦስት መቶ ሺህ እስከ አራት መቶ ሺህ የሚሆኑ ሰዎች ወደ ባርነት እንዲገቡ ተደርገዋል” ሲሉ የኮሚቴው ሊቀመንበር ማይክ ስሚዝ ለቪኦኤ ገልፀዋል፡፡ ሪፖርቱን “ሙሉ በሙሉ የተበላሸ፣ ወይም የተዛባ፤ ሙያዊ ጥራት የሌለውና የአንድ ወገን ሃሣብን ብቻ የያዘ ነው” ሲሉ የኤርትራ ፕሬዚዳንት አማካሪ የማነ ገብረአብ አጣጥለውታል፡፡ የማስረጃ ዶሴዎችን ማሰባሰባቸውን የሚናገሩት መርማሪዎች ግን የኤርትራን ጉዳይ ወደ ዓለምአቀፉ የወንጀል ችሎት እንዲመራ ለመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
ለዝርዝሩ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ፡፡