በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

'አዲስ አበባን እንደ ባግዳድ'?!


የመንግሥታቱ ድርጅት ጣቱን ወደ አሥመራ አዙሯል፤ አሥመራ "ሁሉም ክስ ሃሰት ነው" ትላለች፡፡

የአፍሪካ ኅብረት የዚህ ዓመቱን የመሪዎች ጠቅላላጉባዔ አዲስ አበባ ላይ ጠርቶ በነበረ ጊዜ የኤርትራ መንግሥት መጠነ ሰፊ ጥቃት ለማድረስ አቅዶ እንደነበረ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታወቀ፡፡

ጥቃቱ በታቀደው መሠረት ተፈፅሞ ቢሆን ኖሮ በሲቪሎች ላይ ጉዳት መድረሱ አይቀር እንደነበር የመንግሥታቱ ድርጅት የሰየመው የሶማሊያና የኤርትራ ቃፊር ቡድን አመልክቷል፡፡

ቡድኑ ኤርትራ ጥቃቱን ለመፈፀም ማቀዷን ከማረጋገጡ ጎን 'የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጣለባትን በርካታ የጦር ማዕቀቦች የሚጥስም ነው' ብሎታል፡፡

ቡድኑ አክሎም የሶማሊያን በርካታ ክፍሎች ከሚቆጣጠረው እሥላማዊ ታጣቂ ቡድን አልሻባብ ጋርም ኤርትራ ግንኙነቷን እንደቀጠለች መሆኗን በባለ 400 ገፅ ሪፖርቱ ላይ አመልክቷል፡፡

ይሁን እንጂ ኤርትራ ለቡድኑ የገንዘብ ድጋፍ እንደማታደርግ ገልፃ ክሡን አስተባብላለች፡፡ ቡድኑ ግን በጥናት ላይ የተመረኮዘው ክትትሉ የሚያሣየው ኤርትራ ለአልሻባብ የምትለግሰው ድጋፍ በፖለቲካና በሰብዓዊ አገልግሎቶች የተወሰነ አለመሆኑን ይናገራል፡፡

ኤርትራ ሶማሊያ ውስጥ ያላት የታጠቁ አማፂ ቡድኖችን የመርዳት ሰፊና ተከታታይ ሚና መሆኑን የመንግሥታቱ ድርጅት ይጠቁማል፡፡

የኤርትራ መንግሥት ጥቃቱን በአዲስ አበባ ላይ ለማድረስ አቅዶ እንደነበር ስለ ሪፖርቱ ለአሜሪካ ድምፅ መልስ የሰጡት የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር አቶ አሊ አብዱ ሲጀመርም ሪፖርቱ የወጣው በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አለመሆኑንና "... በኤርትራ ላይ የተጣለው ማዕቀብ እንዳይነሣ የሚፈልጉ ወገኖች ... የሃሰት መረጃዎችን እየሰበሰቡ የሚያደርጉት መንፈራገጥ ነው" ብለውታል፡፡

የመንግሥታቱ ድርጅት የሶማሊያና የኤርትራ ቃፊር ቡድን ስላወጣው ሪፖርት የባለሙያ ማብራሪያ እንዲሰጡ በአሜሪካ ድምፅ የተጠየቁት ቀድሞ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሣደር፣ ከዚያም በዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የምሥራቅ አፍሪካና የአፍሪካ ቀንድ ጉዳዮች ዳይሬክተር፣ አሁን በጀርጅ ዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ የዓለምአቀፍ ጉዳዮች ፕሮፌሰር ዴቪድ ሺን ስለ ሪፖርቱ እንደሚያውቁ ገልፀው ቡድኑ ሶማሊያ ውስጥ የሚካሄደውን ጉዳይ የሚከታተል እንደሆነ፣ ይህንን ሪፖርት ያወጡት ግን እሥላማዊ ቡድኖችን መርዳትና ሌሎችንም በአካባቢው የሚካሄዱ ጉዳዮችን በተመለከተ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አሳሳቢ የሆኑና ኤርትራ የምትወስዳቸውን እርምጃዎች እንዲከታተሉ ተጠይቀቁ መሆኑን አመልክተዋል።

አምባሣደር ሺን "በዘገባው ውስጥ ያለውን መረጃ ማጣራት፣ ማረጋገጥ ወይም ማስተባበል አልችልም። ዘገባው ውስጥ ያለው መረጃ እራሱን የቻለ ነው። እንደተረዳሁት ከሆነ በጥሩ ሁኔታ የተጠናቀረ ነው፤ የማክለው ግን የለኝም።" ብለዋል፡፡

ቀጥለውም "የዘገባው መረጃ ትክክል ከሆነና፣ እውነትም የኤርትራ መንግሥት የተባለውን ጥቃት አቅዶ ከነበረ፣ የኤርትራ መንግሥት ብዙ መልስ የሚሰጥበት ጥያቄ ይኖራል። ጥቃቱ ሊፈፀምባት ታቀደ ከተባለችው ኢትዮጵያ ሌላ ለአጠቃላይ የአፍሪቃ ኅብረትም ያሳስባል፤ እንደተባለው የጥቃቱ ዒላማ የአፍሪቃ ኅብረት ከሆነ።" ሲሉ አክለዋል፡፡

ምሥራቅ አፍሪካን በቅርብ የሚያውቁ፣ በኃላፊነትም፣ በተመራማሪነትም የሠሩና እየሠሩም ያሉ እንደመሆናቸው ኤርትራ በአካባቢው ላይ ያላትን ሚና ሲገመግሙ "ለዓመታት የተሰበሰቡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ኤርትራ በሶማሊያ የሚንቀሳቀሱ የእስልምና አንጃዎችንና፤ አሁን ደግሞ በቅርቡ አልሸባብን እንደምትረዳ አሣማኝ ምክንያቶች አሉ" ብለዋል።

ይህ ተመሳሳይ ማስረጃም በሶማሊያ አጣሪ ኮሚሽን ዘገባም በዝርዝር መጠቀሱን፣ ለምሳሌም ሰማንያ ሺህ ዶላር የሚሆን ገንዘብ ለአልሸባብ በየዓመቱ መስጠቱን የሚያሳዩ ደረሰኞች መካተታቸውን አምባሣደር ሺን ጠቁመው ይህ አሣማኝ እንደሚመስል፤ ሆኖም እርሣቸው እነዚህን መረጃዎች ማረጋገጥም ዕውቅና መንሳትም የሚያስችል እውቀት እንደሌላቸው ተናግረዋል፡፡

"ከአራት ዓመት በፊት መለስ ብለህ ብታስተውል - አሉ አምባሣደር ሺን - ኤርትራ ለሶማሊያ እሥላማዊ አማፂያን የጦር መሣሪያ እርዳታ ትሰጥ እንደነበረ አሣማኝ መረጃዎች አሉ። በዚህ በቅርቡ በወጣው ሪፖርት የጦር መሣሪያ እርዳታ ሰለመኖሩ የተጠቀሰ ነገር የለም፤ የገንዘብ እንዳታ መኖሩ ብቻ ነው የተተነተነው፡፡"

ቡድኑ የባለሙያዎች መሆኑንና የያዘውን ጉዳይ ካላመነበት ይፋ የሚያደርግ አለመሆኑን የተናገሩት አምባሣደር ሺን ተዓማኒነቱን አረጋግጠው፣ ነገር ግን ትክክለኛም ትክክለኛ ያልሆኑም መረጃዎች ሊደርሱት ስለሚችሉ ሦስተኛ ወገን ቢፈትሻቸው መልካም እንደሚሆን መክረዋል፡፡

በኢትዮጵያና በኤርትራ መንግሥታት መካከል ያለው ግንኙነት ከጦርነቱ ወዲህ የመሻሻል አዝማሚያ እንዳላዩበት አምባሣደሩ ገልፀው ምናልባት አነስተኛ የሆኑ ግጭቶች በድንበሮቻቸው አካባቢዎች ሊከሰቱ የሚችሉ ካልሆነ በስተቀር ሁለቱም ሃገሮች ወደ ሌላ ጦርነት ይገባሉ የሚል ግምትም እምነትም እንደሌላቸው ተናግረዋል፡፡

ለዝርዝርና ተጨማሪ መረጃ ዘገባውን ያዳምጡ፡፡

XS
SM
MD
LG