በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በሦሪያውያን የሚመራ የሽግግር ሂደት መኖር እንዳለበት የተመድ ልዑክ አሳሰቡ


ፎቶ ፋይል - ከሥልጣን የተወገዱት የሦሪያ ፕሬዝዳንት ባሻር አል-አሳድን በሦሪያ በሚገኘው የእስር ቤት መግቢያ በር ላይ ፖስተራቸው ተስቅሎ ይታያል፤ ሦሪያ፣ ደማስቆ
ፎቶ ፋይል - ከሥልጣን የተወገዱት የሦሪያ ፕሬዝዳንት ባሻር አል-አሳድን በሦሪያ በሚገኘው የእስር ቤት መግቢያ በር ላይ ፖስተራቸው ተስቅሎ ይታያል፤ ሦሪያ፣ ደማስቆ

የተባበሩት መንግሥታት የሦሪያ ልዑክ ባሻር አል አሳድን ከሥልጣን ካስወገደው አማፂ ቡድን መሪ ጋራ ደማስቆ ላይ ባደረጉት ውይይት የሶሪያ መር የፖለቲካ ሽግግር አስፈላጊነትን አጽንዖት ሰጥተው ማሳሰባቸውን የልዑኩ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል፡፡

የመንግሥታቱ ድርጅት ልዑክ የጊየር ፔደርሰን ጽሕፈት ቤት ዛሬ ሰኞ ባወጣው መግለጫ ሽግግሩ በጎርጎርሳውያኑ 2015 በተላለፈው የመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ውሳኔ ላይ የተመሰረተ መሆን እንዳለበት አሳስቧል፡፡ የጸጥታ ምክር ቤቱ ውሳኔ በስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ ተዓማኒ፣ ሁሉን አቀፍ እና ከኃይማኖት ነጻ አስተዳደር እንዲመሰረት እንዲሁም አዲስ ሕገ መንግሥት ለማርቀቅ የሚያስችል ሂደት እንዲከናወን በማስከተልም ምርጫ እንዲካሄድ የሚጠይቅ መሆኑን የልዩ ልዑኩ ጽሕፈት ቤት መግለጫው አትቷል፡፡

ፔደርሰን ከአማፂያኑ መሪ አህመድ አል-ሻራ ጋራ ባደረጉት ውይይት “የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለሦሪያ ሕዝብ ሁሉንም ርዳታ ለመስጠት ያለውን ፍላጎት አጽንኦት ሰጥተው መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡

አሕመድ አል-ሻራ የጸጥታ ምክር ቤቱ ውሳኔ ወቅታዊውን የሦሪያን ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ እንዲስተካከል ሃሳብ ማቅረባቸውን የቡድናቸው መግለጫ አመልክቷል።

ዛሬ ሰኞ ቤይሩት የገቡት የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብአዊ ርዳታ ኃላፊ ቶም ፍሌቸር ወደ ደማስቆ እንደሚያቀኑ ተናግረዋል፡፡

በተመሳሳይ የአውሮፓ ኅብረት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ኃላፊ ካጃ ካላስ የኅብረቱ የሦሪያ ልዑክ ዛሬ ሰኞ፣ ለውይይት ወደ ደማስቆ እንደሚጓዙ አስታወቀዋል፡፡ የአልሻራ ቡድን ሀያ ታህሪር አል ሻም በዩናይትድ ስቴትስ እና በሌሎችም በሽብርተኛ ቡድንነት የተፈረጀ ነው፡፡

መንግሥታት ከአማጺያኑ ጋራ እየተነጋገሩ ባሉበት በአሁኑ ወቅት ባለሥልጣናት የቡድኑን በሽብርተኝነት መፈረጅ ጉዳይ እንደገና ለማጤን ፈቃደኛ መሆናቸውን የሚጠቁም ፍንጭ እየሰጡ ናቸው ፡፡ ይሁን እንጂ ጉዳዩን የሚወስነው የቡድኑ ተግባር እንደሚሆን አስጠንቅቀዋል።

የአውሮፓ ኅብረት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ሃላፊ ካጃ ካላስ ብረሰልስ ላይ ለጋዜጠኞች ሲናገሩ "እኛ በቃል ብቻ ሳይሆን በተግባር በትክክለኛው አቅጣጫ ሲሄዱ ማየት እንፈልጋለን" ብለዋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG