ኢቱሪ በተባለችው የኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ግዛት በሲቪሎች ላይ በመድረስ ላይ ባለው ጥቃት ምክንያት የጸጥታ ሁኔታው አሳሳቢ መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታውቋል፡፡
ከጥቂት ቀናት በፊት ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት 55 ሰዎች መገደላቸውንና ባለፉት 20 ቀናት የተገደሉት ስዎች ቁጥር 150 መድረሱን የመንግሥታቱ ድርጅት ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱጃሪክ ትናንት ኒው የርክ ላይ ለዜና ሰዎች ተናግረዋል፡፡ በዛ የሚገኙት ማኅበረሰቦች ዕርዳታና ከለላ ይሻሉ ብለዋል ዱጃሪክ።
በኢቱሪ ግዛት ለወራት በቆየው ሁከት ምክንያት 1.6 ሚሊዮን ሰዎች መኖሪያቸውን ለቀው ሸሽተዋል፡፡
የዓለም ምግብ ፕሮግራም 239 ሺሕ ለሚሆኑ ሰዎች የምግብና የገንዘብ ዕርዳታ ማድረጉንና፣ የመንግሥታቱ ድርጅት የተለያዩ ዕርዳታዎችን በመስጠት ላይ መሆኑን ቃል አቀባዩ ጨምረው ገልጸዋል፡፡