ዲሞክራሲያዊት ኮንጎ ሪፐብሊክ ምስራቃዊ ክፍለ ግዛት ውስጥ በዚህ ሳምንት የተመድን በመቃወም በተካሄደ የተቃውሞ ሰልፍ ላይ ሦስት ሰላም አስከባሪዎች እና በርካታ ሲቪሎች በጥይት መገደላቸው በሚመለከት ከሀገሪቱ ፖሊስ ጋር በጋራ ምርመራ እናካሂዳለን የመንግሥታቱ ድርጅት ተልዕኮ ተጠባባቂ ኃላፊ ገለጹ።
በምህጻረ ቃል ሚኑስኮ ተብሎ የሚጠራው የመንግሥታቱ ድርጅት የዲሞክራሲያዊት ኮንጎ አረጋጊ ተልዕኮ ተጠባባቂ ኃላፊው ኻሲም ዴይኚ ሰላም አስከባሪዎቹ ሲቪሎች ላይ ተኩስ መክፈታቸውን የሚያሳይ ምንም ማስረጃ የለንም ብለው ማን እንደተኮሰ ለማወቅ ከሀገሪቱ ፖሊስ ጋር ሆነን ምርመራ እናካሂዳለን ብለዋል።
ኮንጎ ሰሜን ኪየቩ ክፍለ ግዛት ጎማ ከተማ ውስጥ በሚገኘው የተመድ ግቢ ላይ ድንጋይ ሲወረውሩ እና ቃጠሎ ሲያደርሱ ከነበሩ ሰዎች መካከል ሰላም አስከባሪዎች ሁለቱን በትይት መትተው ሲገድሉ ዘጋቢዎቹ ማየታቸውን ሮይተርስ ከትናንት በስተያ ማክሰኞ ዘግቧል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከአባላቱ የተተኮሰ ጥይት ካለ ለማረጋገጥ የሚያስችለው የምርመራ አቅም ያለው መሆኑ የገለጹት ተጠባባቂ ኃላፊው የአስከሬን ምርመራ በማካሄድ ጥይቶች የሚያወጡ ዶክተር ከኪንሻሳ በማምጣት ላይ ነን ብለዋል። ትናንት ረቡዕም ተቃዋሚዎች ለሶስተኛ ተከታታይ ቀን ከሰላም አስከባሪዎች ጋር ተጋጭተዋል። ሆኖም የመንግሥታቱ ድርጅት ተልዕኮ ኃላፊው ሁኔታው ከቀደመው ቀን ጋብ ማለቱን እና ተልዕኮው በንቃት እየተጠባበቀ መሆንን ተናግረዋል።
ባሁኑ ወቅት ማሊ ጉብኝት ላይ ያሉት የመንግሥታቱ ድርጅት የሰላም አስከባሪዎች ዋና ኃላፊ ዣን ፒዬር ላክሯ ነገ ዐርብ ወደ ኪንሻሳ በመጓዝ ከሀገሪቱ ባለሥልጣናት ጋር ተነጋግረው ወደጎማ እንደሚያመሩ ዜናው አመልክቷል።