የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ ደቡብ አፍሪካ በእስራኤል ላይ ያቀረበችውን የዘር ማጥፋት ክስ ሐሙስ እለት ማዳመጥ ጀምሯል። ክሱን እስራኤል እና ዋና አጋሯ ዩናይትድ ስቴትስ ተቃውመውታል።
የደቡብ አፍሪካ የህግ ቡድን አባላት ሐሙስ እለት በዳኞች ቡድን ፊት ቀርበው ባሰሙት ክርክር፣ የእስራኤል ድርጊት "የዘር ማጥፋት ሂደት" ነው ሲሉ ተናግረዋል።
የፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን ሐማስ እ.አ.አ ጥቅምት ሰባት በእስራኤል ሰላማዊ ዜጎች ላይ ባደረሰው ጥቃት ወደ 1ሺህ 200 የሚጠጉ ሰዎች መሞታቸውን እና 240 ሰዎች መታገታቸውን ተከትሎ እስራኤል እያካሄደች ያለችው የጥቃት ዘመቻም በአስቸኳይ እንዲታገድ ጠይቀዋል።
የደቡብ አፍሪካ የፍትህ ሚኒስትር ሮናልድ ላሞላ ከፍርድ ቤቱ ውጪ ባደረጉት ንግግር "በጋዛ እየደረሰ ያለውን የዘር ማጥፋት ለመከላከል መንግስታችን ወደ አለም አቀፉ ፍርድ ቤት ቀርቧል" ያሉ ሲሆን፣ "ለፍትህ ያለው ቁርጠኝነት እና በፍልስጤም የሚደርሰውን አረመኔያዊ ጭፍጨፋ ማስቆም፣ ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የወል እሳቤ ጋር ጥልቅ ተዛምዶ አለው" ብለዋል።
ደቡብ አፍሪካ እስራኤል እ.ኤ.አ. በ1948 የወጣውን የዘር ማጥፋት ስምምነት ጥሳለች በማለት የምትከራከር ሲሆን ጥቃቱን ከ30 ዓመት በፊት በሩዋንዳ ከተፈፀመው የዘር ማጥፋት ጋር ታመሳስላለች።
ክሱን መሠረተ ቢስ ነው በማለት የምታጥለው እስራኤል በበኩሏ፣ ክርክሯን አርብ እለት ለፍርድቤቱ እንደምታቀርብ የተገለፀ ሲሆን፣ ዳኞች ብይን ለመስጠት ግን አመታት ሊወስዱ እንደሚችሉ ተጠቁሟል።
መድረክ / ፎረም