የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሶማሊያ ድጋፍ ተልእኮ ኃላፊ ካትሪዮና ሌንግ ትላንት ለፀጥታው ምክር ቤት ባሰሙት ንግግር "አንዲት ሃገር ረዥም ጊዜ ከዘለቀ ግጭት ወጥታ ለሕዝቧ መሆን እና ብሎም ለአካባቢው አገራት በጎ ኃይል ልትሆን እንደምትችል ሶማሊያ እያሳየች ነው” ብለዋል። ባለፈው የአውሮፓውያኑ 2023 የታህሳስ ወር መጀመሪያ በተካሄደው የሶማሊያ የፀጥታ ጉዳዮች ጉባኤ የቀረበውን ‘ወሳኙን የሶማሊያ የፀጥታ ጉዳዮች ፍኖተ ካርታ’ መጠናቀቅ ጨምሮ የሶማሊያ ፌዴራል መንግስት ባለፉት ቅርብ ወራት ውስጥ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ተግባራት በማሳካት ረገድ ጠንካራ መሻሻል ማሳየቱን ተናግረዋል።
ኃላፊዋ አያይዘውም ባለፈው የጥቅምት ወር ለምክር ቤቱ ካቀረቡት የመጨረሻው መግለጫቸው ወዲህ፡ ሶማሊያ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት - ኢጋድ አባልነት ማግኘቷን፣ ‘ከፍተኛ ዕዳ ያለባቸው ድሃ ሀገራት ተነሳሽነት’ የተባለውን ውጥን ማጠናቀቅ ከምትችልበት እርከን ላይ መድረሷን እና እንዲሁም ለዓመታት ተጥሎባት የቆየው የጦር መሳሪያ ማዕቀብ እንዲነሳ ማድረጓን፤ አሁን በቅርቡ ደግሞ እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር ከ2025 እስከ 2026 ባለው ጊዜ በፀጥታው ምክር ቤት ውስጥ መቀመጫ ለማግኘት የአብዛኛውን የአፍሪካ ህብረት ስራ አስፈፃሚ ምክር ቤት አባላት የይሁንታ ድምጽ ማግኘቷን አመልክተዋል።
“እነዚህ በጣም ጉልህ የሆኑ ተጨባጭ ስኬቶች ናቸው” ያሉት የመንግስታቱ ድርጅት የሶማሊያ ድጋፍ ተልእኮ ኃላፊ፤ በተጨማሪም የሶማሊያ መንግስት የአገሪቱን የደህንነት ጥበቃ ኃላፊነት በባለቤት ሙሉ በሙሉ ለመረከብ የሚያስችል የሽግግር እቅድ ማቅረቡን ተናግረዋል። የሚደርሱትን የሽምቅ ጥቃቶች ለመከላከልና እንዲሁም የተረጋጋ እና የበለፀገ መጭ ጊዜ በሶማሊያ እውን ለማድረግ የፌደራል መንግስቱ የያዘውን ጥረት ለመደገፍ የሶማሊያ ዓለም አቀፍ አጋሮች ያላቸውን የጋራ ፍላጎት ማሳየታቸውንም፡ ሌንግ አክለው አስረድተዋል።
መድረክ / ፎረም