የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዥ ትናንት እሁድ ባደረጉት ጥሪ፣ በቡርኪና ፋሶ፣ ጊኒና ማሊ የሚገኙ አምባገነን መሪዎች ሥልጣንን ለሲቪሎች በአስቸኳይ እንዲያስረክቡ አሳሰቡ፡፡
ዋና ጸሃፊው ይህን ያሳሰቡት፣ ከሴኔጋል ፕሬዚዳንት ማኪ ሳል ጋር፣ በዳካር ተገናኝተው ከተነጋገሩ በኋላ ነው፡፡
ጉተሬዥ ህገ መንግሥታዊ ሥርዓት ወደ ቦታው እንዲመለስ፣ ሥልጣንን ያላግባብ ከጨበጡ ከሶስቱ አገራት መሪዎች ጋር በቀጣይነት ለመነጋገር መስማማታቸውንም አስታውቀዋል፡፡
ከጅሃዲስቶቹ አማጽያን ጋር በሚያደርጉት ትግል፣ ችግር ውስጥ መሆናቸው የሚታወቁት ሦስቱ የሳህል አገሮች፣ ማሊ፣ ጊኒንና ቡርኪናፋሶ፣ በቅርቡ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ተካሂዶባቸዋል፡፡
የሴኔጋሉ ፕሬዚዳንት ማኪ ሳል፣ ኤካዎስ የተባለው የምዕራብ አፍሪካ አገሮች ህብረት የወቅቱ ሊቀመንበር መሆናቸው ተመልክቷል፡፡