ዋሺንግተን ዲሲ —
በዓለም ዙሪያ በኮቪድ-19 ምክንያት የሞቱት ሰዎች ቁጥር ከአንድ ሚሊዮን ማለፉን የዩናይትድ ስቴትሱ ጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ የወረርሽኙ መረጃ ማዕከል አመለከተ።
በኮሮናቫይረስ የተያዙት ሰዎች ቁጥር ደግሞ ከሠላሳ ሦስት ሚሊዮን አሻቅቧል። የዩናይትድ ስቴትስ የቫይረሱ ተያዦዋ ቁጥር ባለፈው ሳምንት ከሰባት ሚሊዮን ማለፉ ሲታወስ ህንድ በትናንትናው ዕለት ከስድስት ሚሊዮን አልፎ ዩናይትድ ስቴትስን በሁለተኛነት እየተከተለች ናት።
የዓለም የጤና ድርጅት በኮቪድ-19 ምክንያት የሞቱት ሰዎች ቁጥር ከተጠቀሰውም ሳይበልጥ እንደማይቀር አመልክቷል።
የድርጅቱ የአጣዳፊ ጉዳዮች ዋና ኃላፊ ዶ/ር ማይክ ራያን ጄኒቫ ላይ በሰጡት ቃል በቫይረሱ ስለተያዙት ወይም ስለሞቱት ሰዎች የሚወጡት አሃዛዊ ሪፖርቶች በተጨባጭ ካለው ያነሰ መሆኑ እንደማይቀር ነው የገለጹት።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትረምፕ አንድ መቶ ሃምሳ ሚሊዮን የኮቪድ-19 ፈጣን መመርመሪያዎችን እናቀርባለን ሲሉ ቃል ገብተዋል።
ፕሬዚዳንቱ ከአሁን ቀደም የቫይረሱ ተያዦች ቁጥር ያሻቀበው በየጊዜው ምርመራ እየተደረገ ተጋላጮች ስለሚገኙ ስለሆነ ምርመራው ዝግ እንዲል እፈልጋለሁ ብለው እንደነበር ይታወሳል።