የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸኃፊ አንቶንዮ ጉቴሬዥ የኮቪድ-19 መዛመትን በመላ ሃገሮች ለመቆጣጠር እንዲቻል፣ የተባበረ አሰራር እንዲፈጠር ባለፍው መጋቢት ወር፣ ሃሳብ ያቀረቡ ቢሆንም፣ 20 በኢንዱስትሪ የበለጸጉት ሃገሮች አልመተባበራቸው ያሳዝናል ብለዋል።
ጉቴሬዥ ከአሶሼትድ ፕሬስ የዜና አገልግሎት ጋር ባደርጉት ቃለ መጠይቅ፣ ቡድን ሃያ በመባል የሚታወቁት፣ በኢንዱስትሪ የበለጸጉት ሃገሮች፣ በመጪው ወር ጉብኤ በሚያደርጉበት ወቅት፣ ዓለማቀፉ ማኅበረሰብ ቫይረሱን ለመታገል፣ በበለጠ መተባበር እንደሚያስፈልግ ይረዳል የሚል ተስፋ እንዳላቸው አስገንዝበዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ የቫይረሱን መዛመት ለመቋቋም፣ ተባብሮ መስራት እንደሚያስፈልግ አጥብቆ ይማጎታል። የቫይረሱ የክትባት መድሃኒት እውን ሲሆንም፣ በማንኛውም ቦታ ለማንኛውም ሰው፣ ተመጣጣኝ በሆነ ዋጋ ተደራሽ እንዲሆን፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ይፈልጋል ብለዋል ዋናው ጸኃፊው።
በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ተመራማሪዎች፣ አስተማማኝና ውጤታማ የሆነ የኮቪድ-19 ክትባት ለመፍጥር፣ እየተሯሯጡ መሆናቸው የሚታወቅ ነው። በዓለም ደርጃ ከ1.1 ሚልዮን በላይ የሚሆኑ ስዎች፣ በቫይረሱ ተይዘው ለሞት ተዳርገዋል። ከ41 ሚልዮን በላይ የሚሆኑት ደግሞ በቫይረሱ ተይዘዋል።
በአሁኑ ወቅት፣ ከአንድ ሚልዮን በላይ የቫይረሱ በሽተኞች ያሉባቸው ሀገሮች ቁጥር ሰባት መድረሱ ታውቋል። በቅርቡ እዚህ ደረጃ ላይ የደረሱት፣ ፈረንሳይና ስፔን ናቸው።
ስለኮሮናቫይረስ ጉዳይ የሚከታተለው፣ የጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ ማዕከል በገለጸው መሰረት፣ ከዓለም የበዙ የቫይረስ በሽተኞች ያሏት ዩናይትድ ስቴትስ ናት። ከ8.4 ሚልዮን በላይ ደርሷል። ቀጣይዋ ህንድ 7.76 ሚልዮን፣ ብራዚል 5.32 ሚልዮን፣ ሩስያ 1.45 ሚልዮን፣ አርጀንቲና 1,053,650 የኮሮናቫይረስ በሽተኞች እንዳሉባቸው ታውቋል።
ስድስተኛ የሆነችው ፈረንሳይ 1,041,991፣ ሰባተኛዋ ስፔን ደግሞ 1,026,281 የኮቪድ 19 በሽተኞች አንዳሉባቸዋል ታውቋል።