የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬሽ ነገ፤ ሐሙስ ከዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪና ከቱርክ ፕሬዚዳንት ሬቼፕ ታይፕ ኤርዶዋን ጋር ምዕራብ ዩክሬን ውስጥ እንደሚሰበሰቡ ተገለጠ።
ስብሰባውን የጠሩት የዩክሬን ፕሬዚዳንት መሆናቸውን የመንግሥታቱ ድርጅት ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱዣሪክ ገልፀዋል።
የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላዲሚር ፑቲንና ሦስቱ መሪዎች በጋራ የጥቁር ባህር የምግብ ተነሳሽነት የተባለው መርኃግብር አባላት ሲሆኑ ባለፈው ሐምሌ 15 ኢስታንቡል ላይ የፈረሙት ስምምነት በሩሲያ የማዳበሪያና የምግብ ንግድ ላይ የነበሩትን አንዳንዶቹን እንቅፋቶች ማስወገዱና የዩክሬን እህል ለዓለም ገበያ መቅረብ እንዲጀምር ማስቻሉ ይታወቃል።
ሩሲያ ዩክሬንን ባለፈው የካቲት አጋማሽ መውረሯን ተከትሎ ሁለት መቶ ሚሊዮን ኲንታል እህል መውጫ አጥቶ መቆየቱ በዓለም ዙሪያ የምግብ ዋጋ እንዲያሻቅብ አድርጓል።
ሰማኒያ ሀገሮች አጣዳፊ የምግብ ችግር ላይ መሆናቸውንና በአርባ አምስት ሀገሮች ውስጥ ደግሞ ሃምሳ ሚሊዮን ሰው ቸነፈር አፋፍ ላይ እንደሚገኝ የዓለም የምግብ ፕሮግራም አስጠንቅቋል።
የጥቁር ባህር የምግብ ተነሳሽነት የጋራ ቅንጅት ማዕከል ሥራውን ከጀመረ ወዲህ ሃያ አንድ መርከቦች አምስት መቶ ስድሣ ሦስት ሺህ ቶን ዕህል ጭነው ከኦዴሳና ከሌሎችም ሁለት ወደቦች ለመንቀሳቀስ ፈቃድ እንዳገኙ ተገልጿል።
ጉቴሬሽ ከፕሬዚዳንት ዜሌንስኪ ጋር የሁለትዮሽ ውይይት እንደሚያደርጉ ቃል አቀባያቸው አመልክተዋል።
ጦርነቱን ለማቆም ፖለቲካዊ መፍትኄ መፈለግና የዓለም አቀፉ አቶሚክ ኢነርጂ ድርጅት አባላት የዛፖሮዥዢያን የኒኩሌር ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ባፋጣኝ መጎብኘት አጣዳፊነት በውይይቱ ከሚነሱት ጉዳዮች መካከል ይሆናሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ዱዣሪክ ጠቁመዋል።