መቀሌ አቅራቢያ ትናንት ተፈፅሟል በተባለ የአየር ድብደባ ሦስት ህፃናት እንደተገደሉና አንድ ሰው እንደቆሰለ የአካባቢው የጤና ሠራተኞች እንደነገሯቸውና ከተማዪቱ ውስጥ ዛሬ ሁኔታው የተረጋጋ ቢሆንም ውጥረት መኖሩን የሰብዓዊ አቅርቦት ሠራተኞቻቸው እንደገለፁላቸው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቃል አቀባይ ፋርሃን ሃቅ ማምሻውን ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
መቀሌ ውስጥ ትናንት ዘግየት ብሎ ደርሷል በተባለ ሁለተኛ የአየር ድብደባ ዘጠኝ ሰው መቁሰሉን፣ ቤቶችና አንድ ሆቴል ላይ ጉዳይ መድረሱን የሚጠቁም ዘገባ እንደደረሳቸው ቃል አቀባዩ አመልክተዋል።
የግጭቱ እየተባባሰ መምጣት ሰብዓዊ ረድዔት አቅራቢዎችን በእጅጉ ያሳሰባቸው መሆኑን የገለፁት ሃቅ “ሁሉም ወገኖች ለዓለምአቀፍ ህግ ግዴታዎች እንዲገዙና ሲቪሎችንና ሲቪል ተቋማትን ከጉዳት እንዲጠብቁ፣ ያለተገደበና ያልተቋረጠ የእርዳታ አቅርቦትም እንዲቀጥል ሰብዓዊ ድርጅቶቹ ጥሪያቸውን በድጋሚ ያሰማሉ” ብለዋል።
መቀሌ ላይ ተፈፅሟል የተባለውን የአየር ድብደባ የመንግሥታቱ ድርጅት እስካሁን አላጣራ እንደሆነ የተጠየቁት ሃቅ ሰዎቻቸው እዚያ እንዳሉና የተቻላቸውን ያህል መረጃ ለማሰባሰብ እየጣሩ መሆናቸውን ገልፀዋል።
ለአሁኑ የሚተማመኑት መቀሌ ያሉ ሰዎችን ጨምሮ በሚደርሷቸው ሪፖርቶች መሆኑን ሃቅ ጠቁመው የአየር ቅኝት መሣሪያ ወይም አሠራር መቀሌ ውስጥ እንደሌላቸውና በዚህም ምክንያት “የሚጠቀሙት አሁን እየተጠቀሙበት ያለውን ቋንቋ እንደሆነ” ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ባስወጣቻቸው በሰባቱ የመንግሥታቱ ድርጅት ባለሥልጣናት ላይ ማስረጃ አቅርባ እንደሆነም ሃቅ ተጠይቀዋል።
“ከኢትዮጵያ መንግሥት እስካሁን የደረሰን ምንም ዓይነት ማስረጃ የለም” ብለዋል።